ቀጥታ፡

የአላ ውሃ ወንዝ ድልድይ መልሶ ግንባታ ስራን በ20 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

ወልዲያ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 የአላ ውሃ ወንዝ ድልድይ መልሶ ግንባታ ስራን በ20 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።

የአላ ውሃ ወንዝ ድልድይ መልሶ ግንባታ ስራ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ስራው መጀመሩን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድዮችና ስትራክቸር ስራዎች ዳይሬክተር ኢንጂነር ጌትነት ዘለቀ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ድልድዩ 108 ሜትር ርዝመትና አራት ነጥብ ሁለት ሜትር ስፋት እንዳለው ያመለከቱት ኢንጅነር ጌትነት ከ20 ቀናት በኋላ ግንባታውን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ስራ ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የድልድዩ መልሶ ግንባታ ስራው ከ41 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት እየተከናወነ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም