በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን- የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ - ኢዜአ አማርኛ
በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን- የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደርና ህዝብ ዝግጁ መሆናቸውን የከተማዋ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ተናገሩ።
ከንቲባው በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የፌደራል መንግስትና ህወሓት የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው።
የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት አለባቸው የሚለውን የኢትዮጵያ የጸና አቋም የሚያጠናክር በመሆኑ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆንና መለመድ ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።
ጦርነት ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራን ስለሚያስከትል ለሰላም ትኩረት መስጠት ተገቢ መሆኑን የጠቀሱት ካንቲባው፣ "በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት የሁላችንም ኃላፊነት ነው" ብለዋል።
"አሁን የተደረሰው የሰላም ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል" ያሉት ከንቲባው፣ አብሮነትን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሁሉም የኢትዮጵያ ጫፍ የሚገኙ ዜጎች የሰላምን ዋጋና ለሀገራዊ የልማት ጎዞ ያለውን አስተዋጽኦ በመረዳት ሰላምና አንድነት ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።
"በሰላም እጦት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን ሥነ-ልቦና በማከምና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አብሮነትን ማሳየት ይኖርብናል" ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ፀጋ ሀገር መሆኗን ያወሱት ካንቲባው፣ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመስራት ሰላም ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።