ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ቅዳሜ ለዋንጫ ይፋለማሉ - ኢዜአ አማርኛ
ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ቅዳሜ ለዋንጫ ይፋለማሉ
አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እግር ኳስ ዋንጫ ለፍጻሜ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ቅዳሜ ለዋንጫ ይፋለማሉ። ባለፈው ዓመት ህዳር ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ቅዳሜ መስከረም 19 ቀን 2011 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል። በዕለቱ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ከቀኑ በ10:00 ሠዓት በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ። በግማሽ ፍጻሜው መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በመርታት ነው ለፍጻሜ የደረሰው። ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባ ጅፋር ሊያደርጉት የነበረውን ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በውድድሩ አልሳተፍም በማለቱና በሜዳ ባለመገኘቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥታ የፎርፌ አሸናፊ ሆኖ ለፍፃሜ ማለፉ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እግር ኳስ ዋንጫ መከላከያ ለፍፃሜ ሲደርስ በተከታታይ አራተኛ ዓመቱ ነው።