ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 06/2015 የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት ከህዝብ ተወካዮች ምክር አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያለበትን ደረጃ የተመለከተው ጥያቄ አንዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገለት ብዙ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአገሪቷ ችግር የሚፈታበት አንደኛው መንገድ በሠላማዊ ንግግርና ውይይት መሆኑን ጠቁመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡና የምክር ቤት አባላት ሊደግፉት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ችግር በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንደሚፈታ እምነት አለኝ ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ መፍትሄ አዘል ስራዎች ላይ በማተኮር ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም