ቀጥታ፡

መንግስት በሌብነት ሀገርን እየበዘበዙ ባሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲያካሂድ የቆየውን ምርምራ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6/2015 መንግስት በሌብነት ሀገርን እየበዘበዙ ባሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲያካሂድ የቆየውን ምርምራ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሩቅ ላሉ የሀገር ጠላቶችም ተላላኪ ሆነው እየሰሩ ያሉ አመራሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሌብነት አታካች ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የገጠመንን ሀገራዊ ችግር እንደ እድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አደርገውታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይል በእግር አይሄድም በእጁ ብቻ እንጂ የሚለው የተለመደ መሆኑን በማንሳት ሌብነት ከልምምድ ባሻገር እንደመብት እየተቆጠረ መሆኑ አደገኛ ነው ብለዋል።

ሌብነት የኢኮኖሚ ነቀዝ የእድገት ነቀርሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዲስ አበባ ውስጥ ባለቤት አልባ ፎቅ የተበራከተው በሌብነት በተገኘ ገንዘብ ሰለተገነባ መሆኑንም አክለዋል።

የሌብነት አሳሳቢ ደረጃ መድረስ ላይ በካቢኔ ደረጃ ከፍተኛ ውይይት አንደተደረገበት ብሔራዊ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በምርምራው በሌብነት ላይ ተመስርተው የተገኙ አካላት ዝርዝር ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አንስተዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሌብነትን ለመቀነስና ሌቦችን ለማጋለጥ ራሱን የቻለ የአገልግሎት ቢሮ ተቋቁሞ እየሰራ በመሆኑ መረጃና ሰነድ በማቀበል ሌቦችን ለማጋለጥ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።

ሆኖም መረጃ የቀረበበት ሁሉ ተጨባጭ ማስረጃ ካልቀረበበት እርምጃ ለመውሰድ አስችጋሪ በመሆኑና የፍትሕ ስርዓቱም የሌብነት አደጋ ውስጥ በመግባቱ መንግስትና ህዝብ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

የፍትሕ ስርዓቱ ከፍተኛ ስብራት ውስጥ በመሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና አስፈጻሚው አካል የፍትሕ ስርዓቱ ጠንካራ ሪፎርም እንዲያካሂድ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም