ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መሻገር የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ህዳር 6 ቀን 2015 በኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መሻገር የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ በተያዘው በጀት ዓመትም 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት የማስመዝገብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያን መዘግየት፣ የዋጋ ንረትን፣ በኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ላይ የሚገጠማቸውን የቢሮክራሲ አሰራርና የተደራጀ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር  እንዲሁም መሰረታዊ የሸቀጦች አቅርቦትን በተመለከተ እየተሰራ ያለውን ስራ በተመለከተ ጥያቄ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠሙትን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም እድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በ2014 በጀት ዓመት የገጠውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ተቋቁሞ የ6 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።

የነፍስ ወከፍ ገቢ 1 ሺህ 212 ዶላር መድረሱን ጠቅሰው፤ አጠቃላይ የአገሪቱ ሃብት 126 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም ተናግረዋል።

በዚህም ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትና ከሰሃራ በታች ካሉ አገራትም ሶስተኛው የግዙፍ ኢኮኖሚ በላቤት መሆኑ መቻሉን አንስተዋል።

ይህም በፈተናዎች ውስጥ የተገኘውን እድገት የበለጠ ለማጠናከር የተለያዩ የግብርና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትን 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ለማምጣት የሚያስችል  ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም