ከዚህ ቀደም የተሰረዘው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በነገው ዕለት ይወጣል - ኢዜአ አማርኛ
ከዚህ ቀደም የተሰረዘው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በነገው ዕለት ይወጣል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 05/2015 ከዚህ ቀደም ተሰርዞ የነበረው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በነገው ዕለት እንደሚወጣ የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የዕጣ አወጣጥ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ሃምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በዕጣው ማውጣት ሂደት ውስጥ በገጠመ ችግር ምክንያት መሰረዙ ይታወቃል፡፡
በአሁኑ የዕጣ አወጣጥ ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን ገልጸው፣ ዕጣውን ለማውጣት የተሄዱት ሂደቶችም ገጥሞ የነበረውን ችግር በሚፈታ መልኩ ኃላፊነት ተወስዶባቸው የተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ያስሚን ወሃብረቢ በሰጡት መግለጫ ከዚህ ቀደም ተሰርዞ የነበረው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ነገ ከሰዓት በኋላ ይወጣል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት በሁለቱም የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮግራም በ20/80 18 ሺህ 930 ቤት እና በ40/60 6 ሺህ 843 ቤቶች በድምሩ 25 ሺህ 791 ቤቶች እጣ የሚወጣባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
የቤት ዕጣ ማውጫ ሲስተሙ በአዲስ መልክ ከፍተኛ ልምድ ባለዉ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) እንዲለማ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ሲስተሙ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ቡድን ማለትም ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ እና ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተካተቱበት ቴክኒካል ኮሚቴ በድጋሜ በመፈተሽ ሲስተሙን የማረጋገጥ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡
እስከ አሁን የተደረጉ ሙከራዎችም የተሳኩ ናቸው ብለዋል፡፡
ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረውን የባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች ጉዳይ ምላሽ ማግኘቱን የገለጹት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሽመልስ ታምራት በበኩላቸው ሶስት መቶ ቤቶችን ለነባርና አዲስ ተመዝጋቢዎች በእጣ ለማስተላለፍ ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዕጣ ለሚተላለፉ ቤቶችና ለመሠረተ ልማት ግንባታ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉም ተገልጿል።
በሁለቱም መርሃ ግብሮች በዕጣው የተካተቱ ቆጣቢዎች እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በአግባቡ የቆጠቡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡