ቀጥታ፡

የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ ቀጥታ ተጠቂ ለነበሩት የትግራይ፣ የአማራ እና አፋር ክልል ህዝብ እረፍት የሚሰጥ ነው - የመንግስት የስራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 05/2015 መንግስት ከህወሓት ጋር የደረሰው የሰላም ስምምነት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በጦርነቱ ቀጥታ ተጠቂ ለነበሩት የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ሕዝብ እረፍት የሚሰጥ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተናገሩ።

ጥላቻ፣ በቀልና የክፋት መንገድ እንደ ሀገር እንደማያዋጣን ታሪክ ምስክር እንደሆነም ተገልጿል።

የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በመንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ ተወያይተዋል።

መንግስት ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ ያከናወነው አጠቃላይ ዝግጅት፣ የሰላም ስምምነቱ ሂደትና ጭብጥ፣ የስምምነቱ አንድምታ እና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች የውይይቱ ትኩረቶች ነበሩ።

በመንግስት በኩል ለሰላም የነበረው ቁርጠኝነትና ወትሮ ዝግጁነት እንዲሁም ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ስኬታማነት አስቀድሞ የተደረገው ዝግጅት እጅግ አመርቂ እንደነበር ተመላክቷል።

ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የተደረገው ውይይትም የሰላም ሰምምነቱን አጠቃላይ አንድምታ በሚመለከት የተሟላ ግንዛቤ መያዝ እንዲቻል ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

ስምምነቱ በአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የተደቀነውን አደጋ መቀልበስ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከዚህም ባሻገር ጦርነቱን በዘላቂነት በማቆም ዘላቂ ሰላም መገንባት በሚያስችል ሁኔታ የተፈፀመ እንደሆነ የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ በውይይታቸው አንስተዋል።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ በጦርነቱ ቀጥታ ተጠቂ ለነበሩት የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልል ህዝብ እረፍት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የምታቀነቅነውን ”ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን አቋም በሚያፀና መንገድ የተፈጸመ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ስምምነቱም ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህልና የታሪክ ምዕራፍ መጀመርን ያበሰረ በመሆኑ እንደ አገር ወደ ህገ-መንግስታዊነትና ህጋዊነት የሚመልስ አቅጣጫ በመያዙ አንድምታው የላቀ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎቹ የሰላም ስምምነቱ ስኬታማ እንዲሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት ለከፈሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በከፍተኛ ብቃት አመራር ለሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና በሰላም ሰምምነቱ ሂደት ተሳታፊ ለነበሩ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

"ጥላቻ፣ በቀልና የክፋት መንገድ እንደ አገር እንደማያዋጣን ታሪካችን ምስክር ነው" ያሉት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎቹ፤ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ቁርሾዎችና ህመሞችን ማከም፣ መጪውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የልማት፣ የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መከተል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የሠላም ስምምነቱ እንዳይደናቅፍ ማድረግ ከዚሁ አገራዊ ራዕይ አኳያ መታየት እንዳለበት የመድረኩ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው መክረውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም