የዓለም ምግብ ፕሮግራም የጋምቤላ ክልልን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ ድጋፉን ያጠናክራል

110

ጋምቤላ (ኢዜአ) ህዳር 5 ቀን 2015 የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጋምቤላ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቀደም ሲል በክልሉ ለ155 ሞዴል አርሶ አደሮችና ለ15 ባለሃብቶች የምርጥ ዘርና የምርት ጥራት ማስጠበቂያ ግብዓቶችን ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል።

በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ሚስተር ክላውዲ ጂቢዳር ከክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ጋር በግብርናው ልማትና ስደተኞች ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ተወያይተዋል።

የክልሉን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቀደም ሲል የጀመረውን የምርት ማሳደጊያና የምርት ጥራት ማስጠበቂያ ግብዓቶችን ድጋፍ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በክልሉ ለሚገኙ ስደተኞች ከውጭ  ሲገዛ  የነበረውን የምግብ ፍጆታ ከአካባቢው አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች በመሸመት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጭምር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀብሎ በማስጠለል ረገድ እያሳየ ላለው ቁርጠኝነትም ሚስተር ክላውዲ ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የግብርናውን ልማት ለማገዝ ለአርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ለጀመረው የምርጥ ዘርና ሌሎች የግብዓት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ዘርፉን በማጠናከር በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት ፕሮግራሙ የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።  

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ2014/2015 የመኸር ወቅት ግብርና ልማት ለ155 ሞዴል አርሶ አደሮችና ለ15 ባለሃብቶች የምርጥ ዘርና የምርት ጥራት ማስጠበቂያ ግብዓቶችን ማቅረቡን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሎው ኡቡፕ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም