ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል ባለፈ የህክምና አገልግሎት ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል ባለፈ የህክምና አገልግሎት ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ ነው
ደሴ ህዳር 5/2015 (ኢዜአ) በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል ባለፈ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ማዕከል ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ፡፡
በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት ከ8 ሚሊዮ ብር በላይ በሆነ ወጪ መልሶ የተገነባው የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የሴቶችና ህጻናት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተመርቆ በዛሬው ዕለት ስራ ጀመሯል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ቢሆንም ለውጡ በሚፈለገው ልክ እየመጣ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልና ተጠቂዎች ፍትሕ እንዲገኙ ለማስቻል ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
የችግሩ ተጋላጮች የሚያገግሙበት፤ የህክምናና የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት ሂደትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል የደሴው ማዕከል እንደ አንዱን በማሳያ አንስተዋል፡፡
ማዕከሉ ዩኒሴፍ ከተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በቅንጅት መልሶ መገንባቱን አንስተው ተጠቂዎች በማዕከሉ የህክምናና የምክር አገልግሎት ከማግኘት ባለፈ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፎች እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል፡፡
በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ወኪል ጂያንፍራንኮ ሮቲግሊያኖ በበኩላቸው ድርጅቱ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል ባለፈ ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላም የህክምናና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥቃቱን ለመከላከልና የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በየአካባቢው እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ጥፋተኞችን ለህግ ለማቅረብ አሁንም የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አለማየሁ ናቸው፡፡
በችግሩ ላይ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ ይሁንና አሁንም እየደረሰ ያለው ቁጥር ቀላል እንዳልሆነና ይህን ለመከላከል ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በደሴ ከተማ የተጀመረው ማዕከል ተጠቂዎችን ለማገዝ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረው፤ በቅርቡ ችግሩ በስፋት በተስተዋለባቸው ወልድያ፤ ሰቆጣና ደባርቅ ከተሞችም ለማስገንባት እቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡