ቀጥታ፡

በጃፓን አለም አቀፍ የወዳጅነት ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያ ምርቶቿንና ባህሎቿን አስተዋውቃለች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 05 ቀን 2015 በጃፓን ታቺካዋ ከተማ ህዳር 3 እና 4/2015 በተካሄደ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል የኢትዮጵያን ባህሎችና ምርቶች ማስተዋወቅ መቻሉን በጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

በፌስቲቫሉ ላይ የውጭ ሀገራት ዜጎችና ተቋማት ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርባቸው እንደ አበባ፣ ቡና የቅባት እህሎችን ጨምሮ መልካም ጣዕም ያለውን ቡና ከነባህላዊ አፈላሉ ማስተወዋወቅ መቻሉን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ በተጨማሪም በምግብ ይዘቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በተለያዩ ጥናቶች የተረጋገጠው እና እውቅና የተቸረው ጤፍ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ መቻሉንም ኤምባሲው ገልጿል።

መድረኩን ኢትዮጵያ ያሏትን ባህሎችና ምርቶችን ቱሪስቶችንና ባለሃብቶችን ለመሳብ እና ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እንደመልካም አጋጣሚ ያገለገለ እንደነበርም ታውቋል።

በጃፓኗ ታቺካዋ ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደው የወዳጅነት ፌስቲቫል በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ዜጎችና ተቋማት የሚሳተፉበት ሲሆን የየሀገራቱ ባህልና ምርት የሚቀርብበት አለም አቀፍ መድረክም ነው።

ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ የተካሔደው የወዳጅነት ፌስቲቫል ተሳታፊ ሃገራት ባህሎቻቸውንና ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደተጠቀሙበት ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም