የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ነገ ይጀመራል

978

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 5/2015 17ኛው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ነገ በኢንዶኔዢያ ባሊ ይጀመራል።

ጉባኤው “በጋራ እናገግም በጋራ እንጠንከር” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።ኢንዶኔዢያ በፕሬዝዳንትነት በምትመራው ስብሰባ የዓለም የጤና ስርዓት፣ዘላቂ የኢነርጂ ሽግግር እና የዲጂታል ለውጥ ዋና የውይይት አጀንዳዎች መሆናቸውን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ልማትና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሌሎች ምክክር ይደረግባቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።

ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የሀገራቱ መሪዎች በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢንዶኔዢያ በመግባት ላይ ናቸው።

ቡድን 20 እ.አ.አ 1991 በጀርመን ኮሎኝ ከተማ በእስያ አህጉር የተከሰተውን የፋይናንስ ቀውስ ተከትሎ 20 የዓለም የበለጸጉና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮችና ማዕከላዊ ባንኮችን ለማስተሳሰር ተቋቋመ።

ከምስረታው 10 ዓመት በኋላ ውይይቱ ወደ ሀገራት መሪዎችና መንግስት እንዲያድግ ተደርጓል።

ቡድን 20 አስራዘጠኝ ሀገራት እና የአውሮፓ ሕብረትን በአባልነት ያቀፈ ነው።

አሜሪካ፣ቻይና፣ሩሲያ፣ቱርክ፣ዩናይትድ ኪንግደም፣ሳዑዲ አረቢያ ፣ ካናዳ ፣ ብራዚል ፣ሕንድ፣ደቡብ ኮሪያ፣ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ጣልያን ፣ ጃፓን ፣ ሜክሲኮ አርጀንቲናና ኢንዶኔዢያ አባል ሀገራቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም