አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የልዩ ኒሻን ተሸላሚ ሆነች - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የልዩ ኒሻን ተሸላሚ ሆነች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 5 ቀን 2015 አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የልዩ ኒሻን ተሸላሚ ሆነች።
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የልዩ ኒሻን ተሸላሚ የሆነችው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በስፖርት ክለቡ ውጤታማ ለሆኑ አትሌቶች ሽልማት ባበረከተበት ወቅት ነው።
ኮሚሽኑ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የኮሚሽኑ ስፖርት ክለብ አባላት የማዕረግ፣ የገንዘብና የልዩ ኒሻን ሽልማት አበርክቷል፡፡
ልዩ ኒሻኑ ደግሞ ለጀግናዋ ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተበርክቷል፡፡
የስፖርት ክለቡ ባለፉት 3 ዓመታት 26 ወርቅ፣ 31 ብር፣ 38 ነሃስ በድምሩ 95 ሚዳሊያዎችን፣ 8 ዋንጫዎችንና 47 ዲፕሎማዎችን በውጪና በሀገር ውስጥ ውድድሮች ማግኘቱ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በተሰጣት እውቅናና ሽልማት መደሰቷን ገልፃለች፡፡
ሽልማቱ የማረሚያ ስፖርት ክለብ ወጣት አትሌቶች ጠንክረው በመስራት የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ያበረታታል ያለችው አትሌቷ በተለያዩ የውድድር መስኮች ሁለት ወይንም ሦስት ወርቅ ከተገኘ አንዱ በማረሚያ ቤት አትሌት መሆኑን ገልፃለች፡፡
ኮሚሽኑ ለ34 ስፖርተኞች ከረዳት ሳጅን እስከ ኮማንደር ድረስ የማዕረግ ዕድገት ሲሰጥ፤ ለ19 ስፖርተኞች የገንዘብ እና ለ13 ስፖርተኞች ደግሞ የእርከን ጭማሪና የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል፡፡
ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የተበረከተው ልዩ የሜዳሊያ ሽልማት ከረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ቀጥሎ ለ2ኛ ጊዜ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡