የሰላም ስምምነቱ በጥሩ ሁኔታ ተካሂዶ ስምምነት ላይ ደርሰናል -ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

378

ህዳር 4 ቀን 2015(ኢዜአ) የተጀመረው የሰላም ሂደት በጥሩ ሁኔታ ተካሂዶ ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዥር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

በኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው ልዑክ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል።

በመንግሥትና ህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አዛዥና የህወሃት ታጣቂዎች አዛዥ ስምምነቱ ተፈፃሚ በሚሆነባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በናይሮቢ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ስምምነቱን በሚመለከት በሰጡት መግለጫ የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ያለገደብ በሚቀርብበት ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡የስምምነቱ አፈፃፀም ላይ የጋራ መግባባት በመውሰድ ለተግባራዊነቱ ተፈራርመናል ነው ያሉት፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ አሁን ላይ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብና ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ህዝባዊ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም