ቀጥታ፡

በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመልሶ ግንባታ 21 ሚሊየን ብር ለገሱ

ህዳር 4/2015/ኢዜአ/ ሪያድ እና ጅዳን ጨምሮ በመላው ሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች 21 ሚሊየን ብር ድጋፍ አሰባስበዋል፡፡

ለሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበልየገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰባቸውን በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተደረገው የድጋፍ አሰባሰብ ማጠቃለያና የምስጋና ፕሮግራም ላይ የላቀ ተሳትፎ ላደሩጉ የዳስፖራ አባላት እና አደረጃጀቶች አምባሳደር ሌንጮ ባቲ የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ላደረጉት ወገናዊ ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና እና አክብሮትም ገልጸዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በማውሳት ዜጎች የሰላም ስምምነቱ ከዳር በሚደረስበት አግባብ እና በሰፊው ለሚካሄዱ የመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ ሥራዎች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም