የማኅበረሰብ ስፖርት ጤናማ ትውልድ ከመገንባት ባሻገር ለሰላምና አብሮነት መጎልበት ሚናው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

14

አዲስ አበባ/ኢዜአ/ህዳር 4/2015 የማኅበረሰብ ስፖርት ጤናማ ትውልድ ከመገንባት ባሻገር ለሰላምና አብሮነት መጎልበት ሚናው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለስ ዓለሙ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ "አዲስ አበባ ኅብረ-ብሔራዊት የሰላም ከተማ" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ሁለተኛው ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በአራዳ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለስ ዓለሙ በመርሃ ግብሩ ላይ  ባስተላለፉት መልዕክት ስፖርት ጤናማ ትውልድ ከመገንባት ባለፈ ለሰላምና አብሮነት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የማኅበረሰብ ስፖርት በአካልና በሥነ-ልቦና የዳበረ ትውልድ በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን  ለመገንባት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው በከተማው የተጀመረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ኅብረተሰቡም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ  ጤናውን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል።

የአካል  ብቃት እንቅስቃሴ አሰልጣኝ የሆነችው ፍቅርተ ንጉሤ በበኩሏ የማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርት ጤናማ ዜጋን ከመፍጠር  ባለፈ ሰዎችን የሚያቀራርብ መድረክ ነው ብላለች ።

በመዲናዋ የማህበረሰብ ስፖርት እንዲዳብር የሚመለከታቸው ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

ሶስተኛው ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቦሌ ክፍለ ከተማ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም