ቀጥታ፡

የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የማሳደግ አዎንታዊ ሚና አለው

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 04/2015 በመንግስትና ህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የኢንቨስትመንት አስፈጻሚ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በመድረኩ እንደተናገሩት የሰላም ስምምነቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የውጪ ባለሀብቶችን በብዛት ለመሳብ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከምንም በላይ ሰላም የሚሻ ዘርፍ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከሚሽነሩ፤ የውጪ ባለሀብቶች በአንድ ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ሰላምና መረጋጋት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ በኮቪድና በጦርነቱ የተቀዛቀዘውን የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በቀጣይ ለማካካስ የሚያስችል አመቺ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ባለፈው አመት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ ይህንንም ዘንድሮ ወደ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እቅዱ ተግቶ መስራትን የሚጠይቅና የሰላም ስምምነቱንም እንደ አንድ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ በትኩረት ለመፈጸም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለውጪ ባለሀብቶች ምቹ የሆኑ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ያወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በተለይም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማእድን፣ ቱሪዝምና የአይሲቲ ዘርፍ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በችግሮች ውስጥም ቢሆን የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት አልተቋረጠም ያሉት ደግሞ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እድሪስ አብዲ ናቸው፡፡

በክልሉ በዘንድሮ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 131 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 180 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በመንግስትና ህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትም ለክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አክለዋል።

የኦሮሚያ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጉደታ አበበ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያለ ስጋት እንዲሰማሩ እድል የሚፈጥር ነው፡፡

በክልሉ በበጀት አመቱ 400 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸውን ባለሀብቶች ለማስተናገድ አቅድ መያዙን ጠቁመው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 42 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከ1 ሺህ 700 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ማስተናገድ ተችሏል ብለዋል፡፡

ትናንት ለአንድ ቀን በተሰናዳው በምክክር መድረኩ የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች የተሳተፉ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በክልሎች የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳለጥ በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም