ቀጥታ፡

የሰቆጣ-ኮረም መንገድ መሀል የሚገኘው የጥራሪ ወንዝ ድልድይ የመልሶ ግንባታ ስራ ተጀመረ

ሰቆጣ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 በደረሰበት ጉዳት ፈርሶ የነበረው የሰቆጣ-ኮረም መንገድ መሀል የሚገኘው የጥራሪ ወንዝ ድልድይ የመልሶ ግንባታ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

ድልድዩን  በተገጣጣሚ ብረት ለመገንባት ከጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችና ግብዓት የማንቀሳቀስ ቀጥሎም ቦታውን የማስተካከል ሥራ ሲከናወን መቆየቱን በአስተዳደሩ የድልድይና ስትራክቸር ሥራዎች ዳይሬክተር ኢንጂነር ጌትነት ዘለቀ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የብረት ድልድዩን የመገጣጠም ስራ ደግሞ ከነገ ጀምሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሚሰራው ተገጣጣሚ ደልድይ 42 ሜትር ርዝመትና 4 ነጥብ 2 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ድልድዩ የሰቆጣ ከተማን ከዛታ እና ኮረም ከተሞች እንደሚያገናኝ ያመለከቱት ኢንጂነር ጌትነት መገንባቱም በአካባቢው የንግድና ሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማቀላጠፍ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ለስራው ሎደርና ዶዘር ከነባለሙያዎቹ በመመደብ ድጋፍ መስጠቱን ጠቅሰው፤ ተገጣጣሚ ድልድዩን በ10 ቀናት ወስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቀደሞ የነበረው ድልድይ በጦርነቱ ምክንያት ከፈረሰ በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደቆየ ጠቁመዋል።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር መንገድ መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰለሞን እሸቱ በበኩላቸው፤ የድልድዩ በፍጥነት መገንባት የአካባቢውን ማህበረሰብ የዕለት ተዕለት ስራ ከማቀላጠፍ ባለፈ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች ተደራሽ እንዲሆን የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም