ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ባለው ክፍት ቦታ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ ማገዝ ይገባል-ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 3 ቀን 2015 ህብረተሰቡም ሆነ ተቋማት ባላቸው ክፍት ቦታ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት እንደ ሀገር ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ ማገዝ እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ገፈርሳ ሳይት የገፈርሳ አዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል የተመረተ የጓሮ አትክልት፣ የወተት ከብቶች እርባታና የገብስ ሰብል ጎብኝተዋል።

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ እንዳሉት፤  በማዕከሉ የሚመረተው የጓሮ አትክልት ሰራተኞች፣ ታካሚዎችና ህብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ያግዛል።

ህብረተሰቡ ባለው ክፍት ቦታ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ቢያለማ እንደ ሀገር ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

የጤና ተቋማት ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ በክፍት ቦታዎች አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት ስራቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦችም ባላቸው ክፍት ቦታ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና ህብረተሰቡ ጤናማ አመጋገብ እንዲከተል ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባቸዋል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ችግር የሆነውን የመቀንጨር በሽታ ለማስቀረት ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ተቋማት ጥቅም ላይ ባልዋሉ በርካታ ክፍት ቦታዎች አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ችግሩን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማህበራዊ ልማት፣ የባህልና እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ እንደ ሀገር ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት የጓሮ አትክልት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከሉ የለማው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ታደሰ በገፈርሳ አዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል በሰባት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ እየተሰራ ያለው የልማት ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕከሉ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በሌሎችም ሰብሎች ከ800 ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም