የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ማህበራዊ ስብራት ለመጠገን እድል ይሰጣል - የተመድ የስደተኞች ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ማህበራዊ ስብራት ለመጠገን እድል ይሰጣል - የተመድ የስደተኞች ተቋም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 3/2015 "የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዱ ወገኖችን ማህበራዊ ስብራት ለመጠገን እድል ይሰጣል" ሲል የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን(ዩኤንኤችሲአር) አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዱ ዲያን ባልዴ ለኢዜአ እንዳሉት፣ስምምነቱ ዜጎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ከመመለስ ባለፈ ብቻ በጦርነቱ የተጎዱ የትምህርት፣የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
በጦርነቱ ሳቢያ የተጎዱ ወገኖችን ማህበራዊ ስብራት ለመጠገን እድል የሚሰጥም ነው ብለዋል።
ድርጅቱ ስምምነቱ በሚፈጥረው ሰብአዊ ድጋፍን ተደራሽ የማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች በመጠቀም በአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ለዚህም ዩኤንኤችሲአር ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በቅርበት ይሰራል ነው ያሉት ተወካዩ።
የተመድ የስደተኞች ተቋም ከኢትዮጵያ መንግስት በተጨማሪ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ደርጅቶች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን መደገፉን ይቀጥላል ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሰብአዊ አቅርቦት ኮሪዶር ክፍት መደረጉም የእርዳታ ድርጅቶች ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በትግራይ፣አማራና አፋር ክልሎች ያሉ ዜጎች በጦርነቱ ከደረሰባቸው ቀውስ ለመታደግ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል፤ ከዚህም አኳያ የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉም ነው የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ተወካይ የገለጹት ።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ርዳታ ተደራሽ ለማድረግ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ክፍት መደረጉን ትናንት ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች የሰሜን ኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።