በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችንና አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል-የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችንና አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል-የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 3/2015 በመንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆንና በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን እንዲሁም አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲወጣ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
የሃይማኖት አባቶቹ የሰላም ስምምነቱ እውን እንዲሆን ቤተ-እምነቶች ፀሎትና ምህላ ሲያደርሱ እንደነበር አስታውሰው፤ ለተፈጸመው የሰላም ስምምነት መጽናትም ምዕመናን ጸሎታቸውን እንዲያበረቱ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የቅርስ ጥበቃ ቤተ-መጻህፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ኃላፊ መላዕከ ሰላም ቆሞስ ዶክተር አባ ቃለፅድቅ ሙሉጌታ "ሰላም የክርስትና አስተምህሮ ግብ ነው" ይላሉ።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ካሊድ መሀመድ "እስልምና ከስያሜው ጀምሮ ሰላም የአስተምህሮው መሰረት ነው" ብለዋል።
ሰላም በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች የየቀኑ የአምልኳቸው አካል የሆነ፤ ለሰው ልጆች የተሰጠ የከበረ ዋጋ ያለው እንደሆነ አባቶች ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ጉለሌ አስኮ የቅዱስ ፍራንሲስኮስ ቤተክርስትያን ቆሞስ አባ ፍስሐ ታፈሰም ሰላም የቤተክርስትያኗ አስተምህሮ ማዕከል መሆኑን ያስረዳሉ።
የሃይማኖት ተቋማት ሰላም እንዲመጣ ፀሎትና ምህላ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊና የኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን መምህር መጋቢ ታምራት አበጋዝ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ምዕመናን በጸሎታቸው መበርታት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን እና ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረትም ህዝቡ የሚችለውን እገዛ የማድረግ ሃይማኖታዊና ሰዋዊ ግዴታ እንዳለበት ተናግረዋል።
ዘላቂ አገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ወገን ለይቅርታና ዕርቅ ቅድሚያ እንዲሰጥ፤ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።
በማህበራዊ ትስስር ገጾች ጥላቻንና መለያየትን የሚሰብኩም ሰዎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው አንድነትንና ሰላምን እንዲሰብኩ የሃይማኖት አባቶቹ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አብሮነታችን እንዲጠነክርና ሰላማችን እንዲጸና ምዕመናኑም የጀመረውን ጸሎትና ምህላ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶችም ምዕመናን ስለ ሰላም፣ ዕርቅና ይቅርታ እንዲተጉ በስብከትና ትምህርቶቻቸው ማስገንዘብ ይገባቸዋል ብለዋል።