የተመድ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተወካዮች የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን የስራ እንቅስቃሴን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የተመድ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተወካዮች የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን የስራ እንቅስቃሴን ጎበኙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ መብት ተወካዮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን የስራ እንቅስቃሴን ጎበኙ።
ጉብኝቱን ያደረጉት የተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ማርሴል አክፖቮ እና በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተመድ ልዑክ (ሞኑስኮ) የሰብአዊ መብት ኦፊሰር ፔሪ ምቢቦንግ ናቸው።
ተወካዮቹ የፌዴራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤትንና ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ ባለፉት አራት አመታት የተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
የተቋሙ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በዲጂታላይዜሽን የተከናወኑ የምርመራ ስራዎችን ተወካዮቹ የጎበኙ ሲሆን መምሪያው በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
የተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ማርሴል አክፖቮ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከተቋማዊ ለውጡ በፊት በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በተቋሙ ቅሬታዎች ይነሱ ነበር ብለዋል።
አሁን በምርመራ ሂደት ላይ የሚታየው የሰብአዊ መብት አያያዝ ዓለም አቀፍ መስፈርትን የተከተለ መሆኑንና ተጨባጭ ለዉጦች መኖራቸውን እንደተገነዘቡ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
የተመድ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተወካዮች ተቋሙ እያደረገ ያለውን የማሻሻያ ስራ እንደሚደግፉ ቃል መግባታቸውንም አመልክቷል።
የአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ የዓለም ዓቀፍ የኦፕሬሽን ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሬይሞንድ ዱዳ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።