በክልሉ 250 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ የአኩሪ አተር እየተሰበሰበ ነው

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በ250 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የለማ የአኩሪ አተር ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አበበ አናጋው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ እየተሰበሰበ ያለው የአኩሪ አተር ሰብል ምርት በ2014/2015 የመኸር ወቅት የለማ ነው።

በአሁኑ ወቅት ምርቱ እየተሰበሰበ ያለው ለአኩሪ አተር ልማት ተስማሚ በሆኑ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በአዊና ሌሎች ቆላማ የክልሉ አካባቢዎች መሆኑን ገልጸዋል።

የምርት አሰባሰቡ ብክነትን በሚቀንስ መልኩ መሆኑን ገልጸው እስካሁንም በአጠቃላይ ከለማው ከ77 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የነበረ ሰብል መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ቀሪ ምርቱንም ከብክነት በጸዳ መልኩ በጥራት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ አበበ ያመለከቱት።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በመኸሩ ወቅት በባለሀብቶች እና በአርሶ አደሮች በአኩሪ አተር የለማው መሬት ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከለማው ጋር ሲነጻጸር በ160 ሺህ ሄክታር ብልጫ አለው።

ሰብሉን ዘንድሮ በስፋት ማልማት የተቻለው በክልሉ የተቋቋሙ የዘይት ፋብሪካዎችን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ለማቃለልና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።

"በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ ባለሀብቶች ያመረቱትን ምርት ለኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው" ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም በቅርበት ሆነው ለአርሶ አደሩ ተገቢ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

"በቀጣይ ለኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የአኩሪ አተር ልማቱን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሙላቱ አስረሳ ካላቸው 10 ሄክታር መሬት 4ቱን በአኩሪ አተር ሰብል በመሸፈን ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ መሰራታቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደር እንደሻው ማሩ በበኩላቸው በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት የአኩሪ አተር ሰብል በአሁኑ ወቅት አያያዙ የተሻለ መሆኑና ከ70 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ 877 አልሚ ባለሃብቶች እና ከ122 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በአኩሪ አተር ልማቱ መሳተፋቸው ታውቋል።

በክልሉ በአኩሪ አተር ሰብል ከለማው መሬትም ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም