የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ሕብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን መተግበር ይገባዋል - የጤና ሚኒስቴር

280

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ሕብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር ራሱን እንዲጠብቅ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

አጎበር መጠቀም፣ የመኖሪያ ስፍራዎችን ንጽሕና መጠበቅና የጸረ ወባ ኬሚካል ማስራጨት በወባ ትንኝ ከመነከስና በበሽታው ከመያዝ የሚታደጉ መንገዶች እንደሆኑ ይታወቃል።

በጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ቡድን መሪ የሆኑት ጉዲሳ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በተለያዩ አካባቢዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በተካሔዱ ተግባራት ስርጭቱን ለመቀነስ ተችሎ የነበረ ቢሆንም መልሶ የማገርሽት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ገልፀዋል።

ለአብነትም በ2015 የመጀመሪያው ሩብ አመት በአጠቃላይ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ምርመራ አድርገው 648 ሺ 127 ሰዎች ላይ የወባ በሽታ እንደተገኝባቸው ገልፀዋል።

የበሽታው ስርጭት በተለይ በአማራ፤ በኦሮሚያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ መታየቱን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በሩብ ዓመቱ የወባ በሽታን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንፃር የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በስፋት መስራቱን ገልፀዋል።

ወቅቱ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ የሚከሰትበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ሊጠብቅ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

በተለይም ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች በመኝታ ሰዓት አጎበርን በመጠቀም በወረርሽኙ ከመያዝ ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸው ነው የተናገሩት ፡፡

ህብረተሰቡ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ የሚል ስሜት፣ ራስ ምታት፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ሕመም፣ የመገጣጠሚያ ሕመም፣ ድካም፣ የልብ ምት መፍጠን፣ ምቾት ማጣት እና ሳል ሲከሰት የወባ በሽታ ምልክቶች በመሆናቸው በአቅራቢያ 

በሚገኝ ጤና ጣቢያ መሄድ እና ምርመራ ማድረግ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም