መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ምርታችንን በማዘመን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንድንቀላቀል ዕድል ፈጥሮልናል- የማዕድን አምራቾች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ምርታችንን በማዘመን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንድንቀላቀል ዕድል ፈጥሮልናል- የማዕድን አምራቾች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ምርታቸውን በማዘመን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ዕድል እንደፈጠረላቸው የማዕድን አምራቾች ገለጹ፡፡
በማዕድን ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ከ270 በላይ አምራች ኩባንያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
የማዕድን አምራቾች ለኢዜአ እንዳሉት በመዲናዋ እየተካሄደ ያለው ኤክስፖ ምርታቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር የሚፈጥር ነው፡፡
በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት የሚገቡበትን ዕድል ለመፍጠር፤ የምርት ጥራትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችና ሙያተኞችን ለመተዋወቅ አግዞናል ብለዋል፡፡
የማዕድን ምርቶችን በዘመናዊ መንገድ ጥራትና መጠናቸውን በማሻሻል ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ዕድል እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ አቅም ለመፍጠር የሚያስችልና በዘርፉ የተሰማሩ ተዋንያንን የሚያነቃቃ መሆኑን በመጠቆም፡፡
መንግስት ለማዕድን ዘርፉ የሰጠው ትኩረት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ከድንጋይ ከሰል አምራቾች ማህበር መካከል አንዱ የሆኑት ብርሃኑ እሸቱ ኤክስፖው የገበያ እጥረት ላላባቸው አምራቾች ትልቅ ዕድል አምጥቷል።
የኔብቱም ትሬዲንግ የማዕድን ማምረቻ ኩባንያ ባለቤት ኢብራሂም ዘገየ በበኩላቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ራሳቸው ተጠቅመው የአገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ የሚችሉበት ዕድልን ይፈጥራሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ በቅባት እህሎችና በቡና ያላትን አለም አቀፍ እውቅና በማዕድኑም ዘርፍ ለመድገም በመንግስት በኩል የተጀመረው ቁርጠኝነት ሊቀጥል እንደሚገባው በመግለጽ።
የማርብል ማምረቻ ድርጅት ባለቤት ወይዘሮ መስከረም እንዳለ በበኩላቸው የተከፈተው ኤክስፖ ምርታችንን ለውጭና ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እገዛ አድርጎልናል ብለዋል።