ቀጥታ፡

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከልን ጎበኙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከልን ጎበኙ።

የስራ ኃላፊዎቹ በኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ገፈርሳ ሳይት የገፈርሳ አዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል ግቢ ውስጥ የተመረተ የጓሮ ልማትን ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ከዶክተር ሊያ ታደሰ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ እና መልካም አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሐይ ጳውሎስ፣ የቡራዩ ከተማ ከንቲባ ጀግናው ግዛው እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ታደሰ ማዕከሉ በ7 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ካለማው የጓሮ አትክልት በተጨማሪ የገብስ ሰብል እንዲሁም የወተት ልማት እያከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት አካል ጉዳተኞች ያለእርዳታ ምርታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የሰው ሰራሽ አካልና ድጋፍ በመስራት አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ አንጋፋ ተቋም ነው።

ባለፈው ዓመት ተቋሙ በአዲስ ተደራጅቶ ስራውን የቀጠለ ሲሆን የገፈርሳ አዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከልም የአገልግሎቱ አንዱ ማዕከል መሆኑን አሰታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም