የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው--ዶክተር ኤልቪስ ፓውል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው--ዶክተር ኤልቪስ ፓውል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 "ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ በተቀናጀ መንገድ ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ ያከናወነችው ተግባር ለመላው አፍሪካ በተሞክሮነት መስፋፋት ያለበት ነው" ሲሉ በአፍሪካ ሕብረት የታላቁ አረንጓዴ ግንብ እርምጃና ዘላቂ የመሬት ሀብት አጠቃቀም አስተባባሪ ዶክተር ኤልቪስ ፓውል ተናገሩ።
27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 27) ጉባኤ ከጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ዝቅተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ስትራቴጂ እና የአረንጓዴ አሻራን አፈጻጸም የተመለከተ የባለድርሻዎች የጎንዮሽ የውይይት መድረክ ትናንት ተካሄዷል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ በሊቀ-መንበርነት ስትመራው የቆየችውና 20 አባል አገራትን ያቀፈው ’የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ሀገሮች ፎረም’ (Climate vulnerable Forum) ሲሆን የኢትዮጵያ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ደን ልማት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
የውይይቱ አላማ እ.አ.አ. እስከ 2050 የሚተገበረው የኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የዝቅተኛ ልቀት አማራጮች ይዘት፣ የትግበራ ስልቶችንና የትግበራ ማስቻያዎችን ለባለድርሻ አካላት ለማስገንዘብና በቀጣይ የአጋርነት ግንኙነትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
በአፍሪካ ሕብረት የታላቁ አረንጓዴ ግንብ እርምጃና ዘላቂ የመሬት ሀብት አጠቃቀም አስተባባሪ ዶክተር ኤልቪስ ፓውል እንዳሉት "ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ በተቀናጀ መንገድ ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ ያከናወነችው ተግባራ ለመላው አፍሪካ በተሞክሮነት መስፋፋት ያለበት ነው" ብለዋል፡፡
ከአጭር ጊዜ አኳያ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመግታት ያከናወነችውን የአረንጓዴ አሻራና የተቀናጀ የአየር ንብረት ለውጥ መግቻ ተግባር ተሞክሮ በውይይቱ ላይ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ አነስተኛ ልቀት እቅድን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዲሁም ከተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በውይይቱ ላይ መነሳታቸውንና በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያ መሰጠቱን የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል።