ቀጥታ፡

ዲጂታል የቡና መረጃ ስርዓት ህገ ወጥ የቡና ንግድን በመቆጣጠር የቡና ኤክስፖርትን ለማሳደግ እያገዘ ነው-ባለስልጣኑ

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 ዲጂታል የቡና መረጃ ስርዓት ህገ ወጥ የቡና ንግድን በመቆጣጠር የቡና ኤክስፖርትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

በተያዘው ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ገልጿል።

በባለስልጣኑ የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኸይሩ ኑሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዲጂታል የቡና መረጃ ስርዓቱ በህገ ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ቡና ለመቆጣጠር እያስቻለ ነው።

የመረጃ ስርዓቱ ከሁሉም የቡና ማዕከላት ለኤክስፖርት የሚላክ ቡና ወደ መዳረሻ ሀገራት እስኪደርስ ድረስ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መሆኑንም አስረድተዋል። 

ስርዓቱ በመዘርጋቱ በ2014 ዓ.ም ብቻ 100 ሚሊዮን ብር የሚያወጣና ወደ ውጪ መላክ የነበረበት 2 ሺህ ቶን ቡና በሀገር ውስጥ በኮንትሮባንድ ሲዘዋወር ተይዞ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመረተው 700 ሺህ ቶን ቡና 50 በመቶ ያህሉ በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ እንደሚውል የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ "ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛ ቡና ተጠቃሚ ዜጎች ያሏት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል" ብለዋል።

ከአራት ዓመት በፊት ወደ ውጪ የሚላከው የኢትዮጵያ ቡና ከ200 ሺህ ቶን እንደማይበልጥ አስታውሰው፣ ባለፈው ዓመት 320 ሺህ ቶን በመላክ አበረታች ውጤት መመዝገቡንና ለውጤቱም የመረጃ ስርዓቱ አስተዋጽኦው የጎላ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ንግድ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በማገኘት ከፍተኛ የቡና ግብይት ለማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቡና በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኤክስፖርት ምርት እስከ 33 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ ያለው ሲሆን ከግብርና ምርቶች ደግሞ 70 በመቶ ድርሻ አለው።

በሀገሪቱ በቡና ልማት 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሰማርተው እንደሚገኙና ኢትዮጵያ በዓለም ጣዕሙ ታዋቂ የሆነው ቡና መገኛ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የ2014 የቡና ኤክስፖርት አፈጻጸምና የ2015 ዕቅድ ትውውቅ ማካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም