ቀጥታ፡

ዳያስፖራው በሩብ ዓመቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 3/ 2015 ዳያስፖራው በ2015 ዓ.ም በጀት የመጀመሪያ ሶስት ወራት በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ማበርከታቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ማኔጅመንት የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ አድርጓል።

በሩብ ዓመቱ ዳያስፖራው በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ከ175 ሚሊዮን ድጋፍ እንዳደረገ ተገልጿል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ስራዎች ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን አገልግሎቱ አስታውቋል።

በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት ሁለት ሺህ በላይ የዳያስፖራ አካውንቶች ተከፍተው ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ እንደሆነና ዳያስፖራው ወደ ሀገር ቤት በሕጋዊ መንገድ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ሬሚታንስ መላኩ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት 26 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ከ700 በላይ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንቶች ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ዲያስፖራው ባለው ሙያ የእውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጸው አገልግሎቱ፤ የዲያስፖራው ሁለንተናዊ ንቁ ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም