የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን የሐረሪ ክልል አመራሮች ገለጹ

ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ማሳያና ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑን የሐረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

አመራሮቹ በስምምነቱ ዙሪያ ባዳረጉት ውይይት ላይ ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ጦርነት ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንደሚያስከትል በተግባር የታየ መሆኑን በመጥቀስ ሰላም አማራጭ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያውያን አንድነትን ለአለም ያሳየ ነው ብለዋል።  

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ በቀለ ተመስገን በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ መሆናችንን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ያለፈውን በመተው የተደረሰው ስምምነት ወደ ፊት የምናገኘው ብዙ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የርዕሰ መስተዳድሩ የሪፎርም አማካሪ አቶ ከተማ ለማ ናቸው።

የክልሉ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ገዛሃኝ በቀለ በበኩላቸው ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው ብለዋል።

የተደረገው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ ክፍል የተከሰተውን ችግር የሚፈታና በቀጣይ ለሚሰሩ የልማት ስራዎች መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም