ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ ኮሪደሮች ለሰብዓዊ ድጋፍ ክፍት መደረጋቸው አቅርቦቱን ለማሳለጥ ምቹ እድል ይፈጥራል - ተመድ - ኢዜአ አማርኛ
ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ ኮሪደሮች ለሰብዓዊ ድጋፍ ክፍት መደረጋቸው አቅርቦቱን ለማሳለጥ ምቹ እድል ይፈጥራል - ተመድ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2015/ኢዜአ/ ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ ኮሪደሮች ለሰብዓዊ ድጋፍ ክፍት መደረጋቸው አቅርቦቱን ለማሳለጥ ምቹ እድል እንደሚፈጥሩ በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም የሰሜን ኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በተለመከተ ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ ተቋማት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ ሁሉም ኮሪደሮች ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ክፍት መደረጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ "መንግስት ለሰብዓዊ እርዳታ ሁሉንም ኮሪደሮች ክፍት በማደረጉ ተደስተናል" ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
መንግስት የወሰደው እርምጃ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ያልተቋረጠ ድጋፍ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው ያብራሩት፡፡
በኢትዮጵያ በተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ሁሉ ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ የሚቻልበት መልካም እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢና አስተባባሪ ተቋማት ለሰሜን ኢትዮጵያ ዜጎች ያልተቋረጠ የምግብ፣ መድሀኒትና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያቀርቡ ተቋማት ሁሉም ኮሪደሮች ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በአማራና አፋር ክልል በኩል ያሉ የየብስ ኮሪደሮችን ጨምሮ የመቀሌ፣ አክሱምና ሽሬ አውሮፕላን ማረፊያዎች ለሰብዓዊ ድጋፈ አቅርቦት ክፍት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአፋር ክልል ከአብዓላ መቀሌ፤ በሁመራ በኩል ሽራሮ፣ ሽሬ አክሱም፣ አድዋ፣ በጎንደር አዲ አርቃይ፣ ማይጸምሪ ሽሬ እንዲሁም የወልዲያ አላማጣ መስመሮች ሁሉም ለሰብዓዊ እርዳታ ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ሰብዓዊ ድጋፍና የህክምና ቁሳቁስ የጫኑ 16 የጭነት ተሽከርካሪዎች በሁመራ በኩል አድርገው ሽራሮ፣ ሽሬ አክሱም አድዋ መግባታቸውንም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የመንግስትን ቁርጠኝነት ተገንዘበው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።