ቀጥታ፡

ሕወሓት የአገሪቱ ችግሮች እንዲፈቱና ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነት አለበት - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 በአገሪቱ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱና ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። "የአንድነትና የጽናት ጉባኤ ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው 13ኛው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ በመቀሌ መካሄድ ጀምሯል። የመላው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ንቅናቄ /መኢብን/ እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) ተወካዮች በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሚከሰቱ አለመረጋጋቶች ሳቢያ ወደ ግጭት እየተገባ ነው። ተስፋ ሰነቅን ስንል አገራችንን የሚፈታተኑና በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ለበርካቶች ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት እየሆኑም ነው። በመሆኑም "መንግስት እየገጠመው ካለው ውስብስብ ችግር ተላቆ ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገባ ህወሃት እንደ አንጋፋ መሪ ድርጅት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል" ነው ያሉት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተወካዮች። በአገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረውና የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ በማድረግ ረገድ ጉባኤው እንደ አገርም አንደ ክልልም ከፍተኛ ሃላፊነት ይጠበቅበታል። ህገ-መንግስቱን በማክበርና በማስከበር በጽናት በመታገል ብሎም ሊስተካከሉ የሚገባቸውና አፋጣኝ መልስ የሚሹ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ህወሃት ጠንካራ ሚና እንዳለው ይታመናል ሲሉም ተናግረዋል። በምስራቅ አፍሪካ አገራት በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም በጅቡቲና ኤርትራ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑንም አውስተዋል። ጉባኤው በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጉልህ ሚና የሚያበረክትበት ብሎም ጠንካራና ወጣት አመራሮችን ወደ ፊት የሚያመጣበት መሆኑን በማመን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በተለይም በጉባኤው ህወሃት ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጠንካራ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እምነታቸውን ገለጸዋል። በጉባኤው የሚጠበቁት ውሳኔዎች አገሪቱ ለገባችበት ችግር የመፍትሄ አካል እንዲሁም አገራዊና ክልላዊ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናዊ ሰላምም የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም