በከፍተኛ ኤሌክትሪክ ሀይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመር ላይ ዘረፋ ሲፈጽሙ የነበሩ ተያዙ -ፖሊስ

83

ወልዲያ ህዳር 2/2015(ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመር ላይ ዘረፋ ሲፈጽሙ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ስምንቱ መያዛቸውን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ግለሰቦቹ በትራንስፎርመሩ ላይ ዘረፋ ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።

የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ቡድን መሪ ምክትል ኢንስፔክተር ፋንታነሽ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ የተያዙት ትላንት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ነው።

ግለሰቦቹ  በቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ለመስኖ ልማት አገልግሎት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያነት የዋለ ትራንስፎርመር  ላይ ዘረፋ በመፈጸም ላይ እንዳሉ መያዛቸውን ተናግረዋል ።

ዘረፋውን ከፈጸሙ መካከል ስምንቱ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ጠቁመው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ለጊዜው መሰወራቸውን አመልክተዋል። ።

የተያዙት ተጠርጣሪዎች በመሩት መሰሩት ከዚህ ቀደም ከዘረፏቸው የሁለት ትራንስፎርመሮች ሙሉ የውስጥ እቃ በቆቦ ከተማ በአንድ ቤት ውስጥ መገኘቱን ምክትል ኢንስፔክተሯ ተናግረዋል።

በቤቱ ውስጥ በተካሄደ ፍተሻም ሌሎች ለኤሌክትሪክ  አገልግሎት  የሚውሉ መሳሪያዎች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኢንስፔክተሯ ለጊዜው የተሰወሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም