የአኗኗር ዘይቤና የአመጋገብ ስርአት የደቀነው ፈተና

49

 የአኗኗር ዘይቤና የአመጋገብ ስርአትን ባለማስተካከል ወደ ህይወታችን የምንጋብዛቸው ገዳይ እንግዶች!

'ሰው ማንን ይመስላል ቢሉ ኑሮውን' እንዲል የሐበሻ ምሳሌ፤ የሰዎች ሕይወት የአኗኗርና አመጋግብ ዘይቤያቸውን መስሏል።

የሰዎች የቀደመ ተፈጥሯዊ አመጋግብ እየተሸረሸረ፤ በዘመን አፈራሽ ኢንዱስትሪዎች በሚመረቱ የታሸጉ ምግቦች እየተዘወተረ መምጣቱ ከአመጋገብ ለውጥ ባለፈ በጤና ላይም የራሱን ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም።

በዚህም የሰው ልጅ በአንድ በኩል የኑሮ ዘይቤውን ሲያቀልል በሌላ መልኩ ግን በተለይም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየተዳረገ መምጣቱን የስነምግብና የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሰዎች የአኗኗር ዘይቤያቸውንና አመጋገብ ስርአታቸውን ባለማስተካከል ወደ ህይወታቸው የሚጋብዟቸው ገዳይ እንግዶች ናቸው።

በኢትዮጵያም ከአኗኗርና አመጋገብ ስርአት መለወጥ ጋር በተገናኘ ዜጎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በስፋት እየተጋለጡ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በኢትዮጵያ 50 በመቶ ገደማ የሚሆነው ሞት የሚመዘገበው ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ነው።

ይህም የአኗኗርና አመጋግብ ስርአታችን እየተቀየረ መምጣቱ እያስከተለ ያለውን ከባድ ጉዳት በገሀድ ያሳያል።

የስነ ምግብ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉትም የካንሰር፣ የደም ግፊት፣ የስኳር እና ልብ እና መሰል ኢ-ተላላፊ በሽታዎች ህሙማንና ሟቾች መበራከት ከጤናማ አመጋገብ፣ አካላዊ እንቅስቃሴና ተያያዥ አኗኗር ችግሮች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

በዲላ ዩኒቨርስቲ የሥነ ምግብ መምህሩ ዶክተር ይሁኔ አየለ ጤናማ አመጋገብ ስርዓት ከምግብ ሰብል አበቃቅል እስከ ምግብ አብስሎ መመገብ ያለውን ዑደት እንደሚያካትት ይናገራሉ።

አሁን አሁን  የሰዎች አኗኗር እና አመጋግብ ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ፤ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የታሸጉ ምግቦች የጤና ጠንቅ እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሙያው እንደሚሉት በተቻለ መጠን የምግብ ሰብሎችን ከኬሚካሎች ንክኪ ነጻ ማድረግ ያሻል።

ከምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የወጡም ሆነ በሌላ መንገድ ተዘጋጅተው ለገበያ የሚቀርቡ እሽግ ምግቦች ጨው እና ጣፋጭ ነገር የሚበዛባቸው በመሆኑ ለኢ-ተላላፊ በሽታዎች መንስኤ ናቸው።

ምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ምግቦቻቸው በተጠቃሚው ህብረተሰብ ዘንድ እንዲዘወተሩ የጨው እና ጣፋጭነት መጠናቸውን ከፍ ባለ መልኩ ይጨምራሉ።

የምግቦቹ አመራረት ሂደትም ምግቦቹ ለሰውነት ያላቸውን ጠቃሚ ንጥረ ነገር እስከማሳጣት የሚደረስ ከመሆኑም ባሻገር በምግቦቹ ላይ የሚጨመረው ኬሚካል የጤና ጠንቅ ይሆናል።

በመሆኑም በፋብሪካዎች የተቀናባበሩ ምርቶች አጠቃቅም ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ካልታከለበት፤ ተጠቃሚዎች በሽታን በገንዘባቸው እየሸመቱ መሆኑን መረዳት ይገባል ነው የሚሉት።

ምግብን በቤት ውስጥ በማዘጋጀትና በመመገብ ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችም የጤና እክል እንዳላቸው ባለሙያው ይናገራሉ።

ለዚህም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ቤት ያፈራውን በሚል ብሂል ለአመጋገብ ስርአት ትኩረት እንደማይሰጡና ተመሳሳይነት ያለው ምግብ እንደሚያዘወትሩ ያነሳሉ።

በሌላ በኩል ከመጠን በላይ /ቁንጣን/ የሚባለው ደረጃ ድረስ መመገብም ሌላ መዘዝ የሚያመጣ መሆኑንም ይናገራሉ።

አሁን አሁን ደግሞ የታሸጉ ምግቦች ተዘውታሪ መሆናቸው፤ ብዙኅኑ ማህበረሰብ ድሃ በሆነበት አገር ችግሩ 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' መሆኑን ይገልጻሉ።

"ምግብ መድሀኒት ነው" የሚሉት ዶክተር ይሁኔ፤ የጓዳ ጥሪትን በተለያዩ አማራጭ በማዘጋጀት መመገብ ሰውነትን በተለያዩ ንጥረ ነገሮች በመገንባት፣ በሽታ መከላከል እንደሚገባ ይመክራሉ።

ለምሳሌ ባቄላን ከሽሮ ባለፈ በበቆልት፣ በቆሎ፤ በንፍሮ፣ ስንዴን በዳቦ፣ በእንጀራና ከሌሎችም ምግቦች ጋር መመገብ መለመድ በስፋት መለመድ አለበት ይላሉ።

በአንድ አካባቢ የሚዘወተሩ ምግቦችን በሌሎች አካባቢዎች ማስፋትም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ያነሳሉ።

ኢትዮጰያ በምግብ አማራጮች ሰፊ ነባር ልምድ ቢኖራትም የአመጋገብ ዘይቤውን አዘምኖና በተለያዩ አካባቢዎች አስፋፍቶ መጠቀም እንዳልተቻለ ነው የሚያብራሩት።

የአመጋገብ ችግር በየትኛውም የኑሮ ደረጃ እንደሚስተዋል ገልጸው፤ ሰዎች ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረትና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እንዳይጋለጡ የአኗኗርና የአመጋገብ ስርአታቸውን መፈተሽና ማስተካከል እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ለልጆች የሚዘጋጁ ምግቦች ላይም ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ያነሳሉ።

በመሆኑም የታሸጉ ምግቦች አጠቃቀምን መፈተሽ፤ ነባር ተፈጥራዊ ይዘት ያላችውና የተለያየ የምግብ አማራጮችን መከተል ለጤናማ ሕይወት ይበጃል ይላሉ።

ቴክኖሎጂ ኑሮን ቢያቃልልም፤ በጤና ላይ ከደቀነው አደጋ ለመዳን አጠቃቅምን ማስተካከልና ከጤና ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም