መንግስት በመላ አገሪቱ የትምህርት ቤቶች ምገባ ስርዓትን ገቢራዊ ለማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ ነው- ትምህርት ሚኒስቴር

22

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2/2015 መንግስት በመላ አገሪቱ የትምህርት ቤቶች ምገባ ስርዓትን ገቢራዊ ለማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የሚመለከታቸው ተቋማትና የልማት አጋሮች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት፣ ዓለም አቀፍ ህጻናት አድን ድርጅት፣ በትምህርት ሚኒስቴርና ከክልል ትምህርት ቢሮዎች አጋርነት አማካኝነት ከታህሳስ 2020 ጀምሮ ለ22 ወራት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው አገር በቀል አካታች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም መስከረም 2022 ተጠናቋል።

መርሃ ግብሩም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌና ሲዳማ  ክልሎች ገቢራዊ ሲደረግ መቆየቱ ዛሬ በተካሄደው የመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ መንግስት የትምህርት ምገባ መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት ላይ ድጋፍ ላደረጉ የልማት አጋሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መንግስት መላው ሀገሪቱ የምገባ መርሐ ግብርን የትምህርት ፍኖተ ካርታው አካል በማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዓለም የምግብ ፕሮግራምና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።

በሰሜን ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት በጦርነቱ ሳቢያ አፋጣኝ ድጋፍ የሚሹበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም ጦርነቱ በነበረባቸው የአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች የትምህርት ቤት የምገባ መርሐግብርን እና የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚሹ ገልጸዋል።

የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም የልማት አጋሮች የጉዳዩን አንገብጋቢነት ተረድተው ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም አቀፉ ህጻናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ጂያኒኔ ሆላውስ በበኩላቸው፤ በ648 ትምህርት ቤቶች ሲደረግ የነበረው የምገባ መርሐ ግብሩ ከ223 ሺህ በላይ ህጻናትን ተጠቃሚ አድርጓል።

በቀጣይ ደግሞ ከ210 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ለአንድ ዓመት የሚቆይ አዲስ ፕሮግራም በተያዘው ወርሃ ህዳር ገቢራዊ መሆን እንደሚጀመር ይፋ አድርገዋል።

በሁለተኛው ዙር ምገባ መርሐ ግብርም በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች ጨምሮ በስድስት ክልሎች በተመረጡ 578 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ እና ሌሎች አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት የቡድን መሪ ዶክተር ሱብራታ ዳሃር፣ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው  ሀገራት ተርታ የምትመደብ መሆኗን አንስተዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ህጻናትን በሚያጋጥሙ ችግሮች ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም