ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ታይላንድን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ በጋራ መስራት ይገባል - አምባሳደር ቼርድኪያት አታከር

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 በኢትዮጵያና ታይላንድ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአየር ንብረት ለውጥ ቋሚ ተወካይና በኬንያ የታይላንድ አምባሳደር ቼርድኪያት አታከር ገለጹ። በምግብና መጠጥ ማቀናበር፣ በኮንስትራክሽን፣ በመኪና መገጣጠሚያ ማሽነሪና በሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ 35 የታይላንድ ኩባያዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ገለጻ ተደርጎላቸዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በሁለቱ አገሮች መካከል የተካሄደው የንግድ ልውውጥ 421 ሚሊዮን ዶላር እንደነበረ ከአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል። ኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ምቹ እንደሆነች የተናገሩት አምባሳደር ቼርድኪያት አታከር በመኪና መገጣጠሚያ ማሽነሪ፣ ኮንስትራክሽን፣ በምግብና መጠጥ ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ምቹ ሁኔታው በአግባቡ መጠቀም የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ''ኢትዮጵያ መስራት የሚችል በቂ የሰው ሃይል፣ ፈጣን እድገት የምታስመዘግብ አገርና በአለም ተወዳዳሪ ገበያ ያላት አገር በመሆኗ የታይላንድ ኩባንያዎች እድሉን እንዲጠቀሙበት እናደርጋለን'' ብለዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማሳደግና የጋራ ተጠቃሚ ለመሆን ታይላንድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት የምትሰራ መሆኗን ጠቁመዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ መስፍን ገብረማርያም በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ቀዝቃዛ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በጤና፣ ምግብና አልባሳት ያለውን የቆየ ግንኙነት ከዚህ በላይ በማሳደግ የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጎልበት ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የኢንቨስትመንት መሰረተ ልማት የታይላንድ ባለሃብቶችም ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል። የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ኤልያስ ገነቲ ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት ገልጸዋል። በኢትዮጵያና ታይላንድ መካከል ካለው 421 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ 45 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ገና ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ በታይላንድ እንዲሁም ታይላንድ ኤምባሲ የሌላቸው መሆኑ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ማነስ አንዱ መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያየ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች ውጤታማ እንደሆኑ ገልጸው፤ የታይላንድ ባለሃብቶችን ይሄንን እድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም