ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተገነባው የሳይንስ ሙዚየም አፍሪካን በሳይንስ ዘርፍ ወደ ፊት ለማሻገር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው-አፍሪካዊያን መሃንዲሶች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2/2015 በኢትዮጵያ የተገባው የሳይንስ ሙዚየም አፍሪካን በሳይንስ ዘርፍ ወደ ፊት ለማሻገር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አፍሪካዊያን መሃንዲሶች ተናገሩ።

8ኛው የአፍሪካ መሃንዲሶች ሳምንትና 6ኛው የአፍሪካ መሃንዲሶች ጉባኤው በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የምህንድስና ባለሙያዎች በጉባኤው ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ባለሙያዎቹ የእንጦጦን ፓርክ፣ የማዕድን ሚኒስቴርና የሳይንስ ሙዚየምን ከጎበኟቸው ቦታዎች መካከል ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አፍሪካዊያን መሀንዲሶች እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ገቢራዊ እያደረጋቸው ያሉ የልማት ስራዎች በአፍሪካም አርአያ የሚሆኑ ናቸው።

በተለይም በቅርቡ ለጎብኚዎች ክፍት የሆነው የሳይንስ ሙዚየም አፍሪካን በሳይንስ ዘርፍ ወደ ፊት ለማሻገር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።

ከጎብኚዎቹ መካከል የኤሌክትሪክ መሃንዲስ የሆነችውና ከጋና የመጣችው ወጣት ፔሻሳ ሳሙዋ ኢትዮጵያን ስጎበኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ ባየሁት ነገር በጣም ተደንቄለሁ ብላለች።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን መጎብኘቷን የተናገረችው ወጣት ፔሻሳ በመሰረተ ልማት ዙሪያ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው ስራ በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ሊተገበር የሚገባው ነው ስትልም አክላለች።

በተለይም በሳይንስ ሙዚየም ውስጥ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማየቷን ገልጻ ፤ይህም በአፍሪካ ሳይንስ እንዲጠናከር እና እንዲያብብ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነም ጠቅሳለች።

የአፍሪካ አገራት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁማ፤ እንደ ሳይንስ ሙዚየም ዓይነት ወጣቶችና ህጻናትን የሚያበረታታ መሰረተ ልማት ሊዘረጉ እንደሚገባም መክራለች።

በኢትዮጵያ ያየሁትን ልምድ ወደ አገሬ ስመለስ ለማጋራት በቁርጠኝነት እሰራለው ስትልም ነው አስተያየቷን የሰጠችው።

ሌላኛዋ ከጋና የመጣችው አስተያየት ሰጪ ኢንጂነር ዴቪድ ኩታናንት በበኩላቸው በሳይንስ ሙዚየሙ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ጋላክሲ፣ ሮቦቲክስን ጨምሮ ስለሳይንስ የጠለቀ ግንዛቤ ለመያዝ የሚያስችል ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ሳይንስ ሙዚየሙ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ሃብት ነው ያሉት ኢንጂነር ዴቪድ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ከዚህ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

ከናይጄሪያ የመጣቸው ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ኢንጂነር ማኪ ኤፊያንሲ ሳይንስ ሙዚየም በአፍሪካ ሀገራት ብዙም ያልተለመደ ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ቀዳሚ መሆን ችላለች ነው ያሉት።

ሳይንስ ሙዚየምን በአጭር ጊዜ ማሳካት እንኳን ባይቻል የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ ትምህርት ወስደው የረጅም ጊዜ እቅዳቸው አካል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የልማት ስራዎች የአገሪቷ መሪዎች የዜጎቻቸውን ህይወት ለመቀየር በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን አመላካች እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም