ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ በፈቃደኝነት ደም መለገስን ባህሉ በማድረግ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዲደርስ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2015 ህብረተሰቡ በፈቃደኝነት ደም መለገስን ባህሉ በማድረግ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዲደርስ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡

አንድ በጎ ፈቃደኛ አንድ ጊዜ የሚለግሰው ደም የሶስት ሰዎችን ሕይወት የማዳን አቅም እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ አገር ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ቢያንስ አንድ በመቶ የሚሆኑት ደም ለጋሽ መሆን እንዳለባቸው ያስቀምጣል።

የአንድ አገር የደም ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ተሟልቷል ተብሎ የሚታሰበውም መደበኛ ደም ለጋሾች ሲኖሩ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያም በመደበኛነት ደም የሚለግሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ማነስ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ዜጎች በሚፈለገው ልክና ጊዜ መድረስ አልተቻለም።

ባለፉት ሦስት ወራትም ደም ይለግሳሉ ተብለው ከተጠበቁ 120 ሺህ ሰዎች መካከል ደም የለገሱት 78 ሺህ 800 ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት አገልግሎቱ ደም መለገስን ባህሉ ያደረገ የህብረተሰብ ክፍል ለማፍራት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡  

በኢትዮጵያ በመደበኛነት ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንና ይህንን ችግር ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በአገሪቱ 490 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸው አገልግሎቱ ይህን ለማሳካት ከትምህርት ቤት ማህበረሰብ፣ ከወጣቶችና ከክልሎች ጋር በጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።   

ለአብነትም በአማራ፣  በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ያለው ተሞክሮ ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር ጥሩ መሆኑን ገልጸው፣ የደም አሰጣጥና አሰባሰብ ሂደቱም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአንጻሩም በአፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ክልሎች ጋር የደም አሰጣጥ ባህሉ አናሳ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ለማስፋት እና ህዝቡ የደም መለገስ ባህሉን እንዲያዳብር እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

አገልግሎቱ አስተማማኝ የሆነ የደም ምንጭ እንዲኖር አሰራር ዘርግቶ በተሻለ መልኩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የደም መለገስ ጥቅምን የተረዳ የማህበረሰብ ክፍል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ግን ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ኀብረተሰቡ ደም መስጠት ህይወት ማዳን መሆኑን በመገንዘብ በየሶስት ወሩ ደም የመስጠት ባህሉን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርበዋል። 

ባለፉት ሶስት ወራት ከ78 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን ጠቁመው ኀብረተሰቡ ደም መስጠት ህይወት ማዳን መሆኑን በመገንዘብ ደም የመስጠት ባህሉን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም