በተለያዩ ዓለም አገራት የሚሰሩ አፍሪካዊያን መሃንዲሶች አፍሪካን መቀየር ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ዓለም አገራት የሚሰሩ አፍሪካዊያን መሃንዲሶች አፍሪካን መቀየር ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2015 በተለያዩ ዓለም አገራት የሚሰሩ አፍሪካዊያን መሃንዲሶች አፍሪካን መቀየር ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
ከጥቅምት 28 ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 8ኛው የአፍሪካ መሃንዲሶች ሳምንት እንዲሁም 6ኛው የአፍሪካ መሃንዲሶች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ጉባኤው የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ከግብ ለማድረስ የአፍሪካ መሃንዲሶች ሚና ላይ ትኩረት አድርጎ መከናወኑን ነው የጉባኤው አስተባባሪዎች የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል መሃንዲሶች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ አፍሪካን በመሰረተ ልማት ለማልማትና እድገቷን ለማረጋገጥ መሃንዲሶች ላይ መስራት ወሳኝ ነው።
አፍሪካዊያን መሀንዲሶች በበርካታ ዓለም አገራት እውቀታቸውን በመጠቀም እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ያላቸውን ልምድና እውቀት በአህጉሪቱ ለሚሰሩ መሃንዲሶች በማካፈል ለአፍሪካ እድገት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በአፍሪካ ውስጥ የሚሰሩ መሃንዲሶች ደግሞ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ጉባኤው በዚህ ላይ አጽንኦት ሰጥቶ መወያየቱንም ነው ያብራሩት።
በአፍሪካ በክህሎት የዳበሩ መሃንዲሶችን ለማፍራት በተለይ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት በጉባኤው መመላከቱንም አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትና መንግስታቱ ድርጅት በዚህ ላይ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው መነሳቱንም ነው የጠቀሱት፡፡
በጉባኤው የአፍሪካ መሃንዲሶች ጥምረት ህብረት ቅርጫፍ ቢሮ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀው ቢሮው ከአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመሆን የሚሰሩ የአቅም ግንባታ ስራዎችን የማስተባበር ሚና እንደሚኖረውም አክለዋል።
እንደ ኢንጂነር ዮናስ ገለጻ፤ የአፍሪካ መሃንዲሶች በተለያዩ የአህጉሪቱ አካባቢ ተዘዋውረው መስራት የሚችሉበት ወጥ የሆነ የስራ ፍቃድ አሰራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከጉባኤው የትኩረት ነጥቦች አንዱ ነው።
ሌላው የጉባኤው አስተባባሪ እና የዓለም መሃንዲሶች ጥምረት ምክትል ፕሬዝዳንት ማርቲን ማኑዋ በበኩላቸው በአፍሪካ መሃንዲሶች ጉባኤ ላይ የሚነሱ ምክረ ሀሳቦች ተቀባይነት አግኝተው ተግባራዊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባኤ ላይም የአፍሪካ መሃንዲሶች ለአህጉሪቱ ማደግ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት ምክረ ሀሳቦች መውጣታቸውንም ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበበ የተካሄደው ጉባኤ የተሻለ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአካል ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡበት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
ቀጣዩ የአፍሪካ መሃንዲሶች ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ በመግለጫው ላይ ይፋ ተደርጓል።