ኢንስቲትዩቱ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ የዶሮ ስጋና እንቁላል ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ የዶሮ ስጋና እንቁላል ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ለዶሮ እርባታ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት ቢኖራትም በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ የህብረተሰቡን የዶሮ ስጋና እንቁላል ፍላጎት ማርካት አልቻለችም፡፡

በተለይ የዶሮ እርባታ በአነስተኛ ቦታ የሚከናወን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎችን በመስኩ እንዲሰማሩ የማድረግ እድል አለው፡፡

ይህን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ደግሞ በዘርፉ በርካታ ስራዎች ሊከናወኑ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዶሮ፣ ማርና ወተት ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገና "የሌማት ትሩፋት" የተሰኘ አገር አቀፍ መርሃ ግብር ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡

"ሌማት" ዶሮ በማርባት፣ ንብ በማነብና የወተት ላሞችን ዝርያ በማሻሻል አርሶና አርብቶ አደሩን ከሸማቹ ጋር በማገናኘት በአጭር ጊዜ የዜጎችን ምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ዓላማ አድርጎ የሚተገበር መርሃ ግብር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የዶሮ ተመራማሪና የብሔራዊ ዶሮ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሚስባህ ሀላዊ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በዓመት የሚገኘው የእንቁላል ምርት ከአፍሪካ አገራት  አማካኝ ምርት አንጻር ዝቅተኛ ነው፡፡

በመሆኑም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ህብረተሰቡ በቂ የዶሮ ስጋና እንቁላል የሚያገኝበት የምርምር ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ደረጃ 220  እንቁላል እንዲሁም በአርሶ አደር ደረጃ ደግሞ በዓመት እስከ 150 እንቁላል መስጠት የሚችሉ "ኮኮክ" የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን በማላማድ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በምርምር ደረጃ 240 እንዲሁም በአርሶ አደር ደረጃ ደግሞ በዓመት እስከ 200 እንቁላል መስጠት የሚችሉ "ዲ ዜድ ዋይ" የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን ለማሰራጨት ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሀገረሰብ ዝርያ ዶሮዎች በዓመት የሚጥሉት የእንቁላል መጠን ከ40 እንደማይበልጥ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የሀገረሰብ የዶሮ ዝርያዎችን በመረጣ ለማሻሻል "ሆሮ" የተባለ የዶሮ ዝርያ መረጣ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሐበሻ ዶሮዎች እንቁላል መጣል ለመጀመር እስከ ሰባት ወር የሚወስድባቸው ሲሆን፤ የተሻሻሉት ዝርያዎች ግን በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ እንቁላል መጣል ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

የተሻሻሉ ዝርያዎች ወንዶች እስከ ሶስት ሴቶች እስከ ሁለት ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሲሆን ነባሮቹ የአርሶ አደሩ የዶሮ ዝርያዎች ወንዶች ከሁለት ሴቶቹ ከአንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም አይበልጡም ነው ያሉት፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአርሶ አደሩን የዶሮ ስጋና እንቁላል አቅርቦት ማሳደግ የሚያስችሉ "ዲ ዜድ ዋይት"፣ "ኮኮክ" እና "ሆሮ" የተባሉ የተሻሻሉ ዝርያዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

በማዕከሉ በዓመት የሚፈለፈለው የዶሮ ጫጩት ከ350 ሺህ እንደማይበልጥ ገልጸው፤ ለዘመናዊ ዶሮ እርባታ አማራጭ ጥሬ እቃዎች ከቀረቡ በዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ጫጩቶችን አራብቶ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ይቻላል ብለዋል፡፡

በደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል የተላመዱና የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ብዜት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ የኢትዮጵያን የእንቁላል ምርት በ20 በመቶ ማሳደግ ይችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ በቂ የዶሮ ስጋና እንቁላል አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከክልል ግብርና ቢሮዎች ጋር በመተባበር የዶሮ ዕርባታ ማዕከላትን በማስፋፋት አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን እንዲያረቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የሚያስችላቸውን የስጋና እንቁላል ዶሮ ዝርያዎች በስፋት እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል ግልጽ አሰራር ተዘርግቷልም ብለዋል፡፡

የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳኘ ሞጆ ማዕከሉ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ማቅረብ የሚችልበት ቁመና ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በዓመት ሁለት ሚሊዩን ጫጩት ማምረት የሚችል ዘመናዊ የዶሮ ጫጩት ማስፈልፈያ መሳሪያ እንዳለው ጠቅሰው፤ በፋይናንስ እጥረትና በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ይህ አቅሙ እስከ 30 በመቶ ዝቅ የሚልበት አጋጣሚ እየተፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለአብነት ባለፈው ዓመት በመኖ እጥረት ምክንያት ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዲወገዱ ለማድረግ ተገደናል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም