ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተፈጠረው ሽርክና ለናይጄሪያ ምርጡ አጋርነት ነው- ሃዲ ሲሪካ - ኢዜአ አማርኛ
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተፈጠረው ሽርክና ለናይጄሪያ ምርጡ አጋርነት ነው- ሃዲ ሲሪካ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2015 ናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገዷ ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የፈጠረችው ሽርክና ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCTA) ጋር የተጣጣመ ምርጡ አጋርነት ነው ሲል የአገሪቱ የአቪዬሽን ሚኒስቴር ገለጸ።
የናይጄሪያ የአቪዬሽን ሚኒስትር ሃዲ ሲሪካ ጉዳዩን አስመልክተው አቡጃ ውስጥ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተደረሰው ሥምምነት ለናይጄሪያ ምርጥ አጋርነት የሚፈጥር ነው።
በአፍሪካ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑ አየር መንገዶች አፍሪካውያን ባልሆኑ ኩባንያዎች እንደሚንቀሳቀሱ ያወሱት ሚኒስትሩ ይህም የአሕጉሪቷን ህዝቦች ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም ብለዋል።
በአንፃሩ በኢትዮጵያውያን የተያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ቀዳሚ ትርፋማ አየር መንገድ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ወረርሸኝ በነበረባቸው ዓመታት ጭምር ጠንክሮ በመስራት ትርፋማ መሆን የቻለ ብቸኛ አየር መንገድ እንደሆነም ገልጸዋል።
ሽርክናው ለ250 ሚሊዮን የናይጄሪያ ህዝብ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ምጣኔ ኃብት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
ሃዲ ሲሪኪ አክለውም የናይጄሪያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በአጋርነት እንዲሰራ መወሰኑ አግባብነት ያለው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
“የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ጭምር ሆኖ ላለፉት 70 ዓመታት አገልግሏል።
በዚህ ዓመት ብቻ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ትርፍ ማግኘት የቻለ አየር መንገድ ነው” ሲሉ የሽርክናውን ጠቃሚነት አብራርተዋል።
“የህዝብ ቁጥር፣ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴና ትራንስፖርት በእጅጉ የተሳሰሩ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም” ያሉት ሚኒስትሩ በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያና ናይጄሪያን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ማስተሳሰር ለአፍሪካ የሚኖረው ትሩፋት የበዛ ነው ብለዋል።
አሁን ባለው አህጉራዊ የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴና ከ 250 ሚሊዮን ለሚልቀው የናይጄሪያ ህዝብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሻለ አገልግሎት ሰጪ ማግኘት ከባድ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስምረውበታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጄሪያ አየር መንገድን 49 በመቶ ድርሻ እንዲወስድ ስምምነት ላይ መደረሱ የሚታወስ ነው።