የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የሠላም ስምምነቱን መንፈስ በመከተል መረጃዎችን ተደራሽ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የሠላም ስምምነቱን መንፈስ በመከተል መረጃዎችን ተደራሽ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2015 የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ከክልል እና የከተማ መሥተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡
የውይይቱ ዓላማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የሠላም ስምምነቱ መርሆችንና ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ የተግባቦት ሥራ እንዲሰራ ለማድረግ ነው፡፡
በውይይቱ ሕዝቡ ወቅታዊና ትክክለኛ የመንግሥት መረጃዎችን እንዲያገኝ በኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ መከወን ስለሚገባው ጉዳይ በተጨማሪ ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግር በሚወገድበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሔደዉን የውይይት መድረክ የመሩት የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ የሚደረጉ የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች የሰላም ስምምነቱን ድንጋጌዎች ያከበሩና የሕዝቦች ወንድማማችነትና አብሮነትን በሚያጠናክር አኳኋን መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የተናበቡ ትክክለኛና ወቅታዊ የመንግሥት መረጃዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን መረጃ የማግኘት ፍላጎት ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ዶክተር ለገሰ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው የኮሙዩኒኬሽን እና የሚዲያ ተቋማት ተናበው ከጥላቸና ግጭት ቀስቃሽ የፀዳ መረጃ ለኅብረተሰቡ በማድረስ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ተግባራዊነት እንዲያረጋግጡ አስገንዝበዋል፡፡
አያይዘዉም የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የተጀመረውን ሀገራዊ የሰላም ሂደት ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዳው ለማድረግ መስራት አለባቸውም ብለዋል ኃላፊው፡፡
ሕዝቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግሥት መረጃዎችን በፍጥነት እንዲያገኝ፣ የሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት እንዲጎለብት፣ በግጭት ሳቢያ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ረገድ ሕዝቡ ወቅታዊ መረጃዎችን አግኝቶ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለማድረግ የተጠናከሩ የኮሙዩኒኬሽን ሥራዎችን እንደሚሠሩም ተሳታፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡