ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋም የዳያስፖራውን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ያሳድጋል ተባለ

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋም የዳያስፖራውን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ። 10 ሺህ የሚጠጉ አባላት ያሉት ማህበሩ የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደገ ያለመ ውይይት መስከረም 19 ቀን 2011 ዓም ሊያካሄድ መሆኑን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል። ዳያስፖራው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለውን ሃሳብና ጥያቄ ይዞ በውይይቱ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል። የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ኢድሪስ መሐመድ እንደገለጹት፤ መንግስት ለዳያስፖራው ትኩረት ሰጥቶ የዳያስፖራ ኤጄንሲ ለመመስረት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የዳያስፖራው ተሳትፎ ለማሳደግ ይረዳል። ኤጀንሲው ተቋቁሞ ወደስራ ስራ ሲገባ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል በምስረታ ሂደቱ ዳያስፖራው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። ዳያስፖራው በገቢዎችና ጉምሩክ አሰራሮች ላይ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችና ችግሮች ለመፍታት ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶች የሚካሄዱ እንደሆነም ጠቁመዋል። ማህበሩ አሁን ከሚያካሂደው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያተኮረ ውይይት በተጨማሪ በሪል ስቴት ኢንቨስትመንትና የመኖሪያ ቤቶች ዘርፍ ላይ በቀጣይ ውይይት ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ማህበሩ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ማህበሩ በውጭ አገሮች በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን መብት ለማስከበር እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ማህበሩ ገልፀዋል። የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም ውይይቱ ዳያስፖራው በአገሪቱ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች የተመለከተ መረጃዎች የሚያገኝበት መድረክ እንደሚሆን ተናግረዋል። በውይይቱ ዳያስፖራው የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ የሚደረጉ ማበረታቻዎችን እና የሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል። በውይይቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር እና የገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሓላፊዎችና ባለሙያዎች እንደሚገኙ አቶ አብርሃም ጠቁመዋል። “አገሪቱ ተስፋ ያላትና በማደግ ላይ የምትገኝ ናት” ያሉት አቶ አብርሃም ዳያስፖራው የሚገጥመውን ችግር ከመንግስት ጋር ተባብሮ እየፈታ በአገሩ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። መንግስት ዳያስፖራው አዲሱን ዓመት በአገር ቤት እንዲያከብሩ ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ወደ አገር መግባታቸውን ማህበሩ አስታውቋል። በውይይቱ ከ750 በላይ የዳያስፖራ አባላት ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም