በዞኑ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ ነው

125

መተማ (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 በምዕራብ ጎንደር ዞን የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል 295ሺህ የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።  

በመምሪያው የወባና ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከታተልና መቆጣጠር ቡድን መሪ አቶ ወርቁ መንግስቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በዞኑ መተማና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች የወባ በሽታ በስፋት ተከስቶ ነበር።

በእዚህም ባለፉት ሦስት ወራት በዞኑ ከ30ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ገልጸዋል።

በወባ በሽታ ከተያዙት አብዛኞቹ በተደረገላቸው ሕክምና ድነው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ይሁንና ዘግይተው ወደ ሕክምና የመጡ 84 ሕሙማን በአሁኑ ወቅት ሕክምናቸውን ተኝተው እየተከታተሉ መሆኑን ቡድን መሪው ገልጸዋል።

የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በዞኑ እየተስፋፋ ያለው የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰትም የቅድመ መከላከል ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ ወርቁ አስታውቀዋል።  

ለእዚህም በቋራ፣ ምዕራብ አርማጭሆ እና በመተማ ወረዳዎች በ90ሺህ 545 መኖሪያ ቤቶች ላይ ኬሚካል መረጨቱን ነው የገለጹት።

የአካባቢ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ወርቁ፣ "በክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ወደዞኑ እየገቡ ያሉ 295 ሺህ አጎበሮችንም ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም