ቀጥታ፡

የችግሯን ያህል ድምጿ ያልጎላው አፍሪካ

በአየለ ያረጋል (ኢዜአ)

የዓለማችን አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔያት ቁንጮ የሚሰኘው የባለድርሻዎች ጉባዔ ወይም 'ኮፕ' በግብጿ የቀይ ባህር ዳርቻ ሻልማ ኤል ሸይክ ከተማ መካሄዱን ቀጥሏል።

ለ27ኛ ጊዜ በአፍሪካ የሚካሄደው ጉባዔው በተለይም የአህጉሪቱ ጉዳይ የሚገዳቸው አካላት ጉባዔውን 'የአፍሪካ ኮፕ' ሲሉት ተደምጠዋል።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ አበርክቶዋ ጉልህ ባይሆንም ተጎጂነቷ ግን ከፍተኛ መሆኑ በገሀድ እየታየ ነው።

በዚህም በርካታ የአፍሪካ መሪዎች በጉባዔው በተለይ በካይ ጋዝን በመልቀቅ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ አገራት የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው የሚለውን አስተጋብተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ 'የዓለም አገራት እጣ ፈንታ ተባብሮ ቀውሱን መግታት፤ ወይም ተያይዞ መስመጥ' እንደሆነ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ዋና ፀሐፊው በተለይም ከችግሩ ይበልጥ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ የአፍሪካ አገራት ይህን ያህል አጽንኦት የሰጡ ግን አይመስሉም።

አክሽን ፎር ዴቬሎፕመንት የተሰኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ሐይማኖት ደሳለኝ፤ ከዚህ በፊት በኮፕ ጉባዔዎች ተሳትፈው ያውቃሉ። በየዓመቱ የሚደረገው ጉባዔ በውጤታማነቱ እየተሻሻለ ቢመጣም በስምምነቶቹ ልክ ግን ቁርጥ ያሉ እርምጃዎች እንዳልተወሰዱ ይናገራሉ።

ታዳጊ አገራትን ክፉኛ እየተፈታተነ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ፤ በበርሃማነት መስፋፋት፣ ሙቀት መጨመር፣ ድርቅ፣ ጎርፍና የዝናብ ወቅት መዛባት በተለይ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች ነገሩ "በእንቅርት ላይ..." ሆኗል ይላሉ።

የፓሪስ ስምምንትን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ ለመቋቋም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የተደረሱ ስምምነቶች በአደጉ አገራት ገቢራዊ እንዳልሆኑም ያነሳሉ።

በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ፈንድ ለአገራት ፈሰስ እንዲሆን በጉባዔዎች የተደረሰው ስምምነትም ከሃሳብ በዘለለ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዳልተደረገም እንዲሁ።

በዚህም የአደጉ አገራት ቃላቸውን አልጠበቁም፤ የገቡትንም ስምምነት ለመተግበር ቁርጠኛ አልሆኑም በማለት ይናገራሉ።

አሁናዊ ሁኔታው የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ አሜሪካን ጨምሮ መላ አውሮፓን ቢፈትንም፤ ለተግባራዊ እርምጃው ግን አልፈጠኑም ነው የሚሉት።

ኢትዮጵያና መሰል ታዳጊ አገራት ደግሞ ይበልጥ ለችግሩ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልፀው፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ግን የተሻለ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ በመጠቆም።  ለአብነትም ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ግንባታ፤ በአረንጓዴ አሻራና በአካባቢ ጥበቃ ያከናወነቻቸውን ስራዎችን በመጥቀስ።

ቀጠና አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ የበርሀማነት መስፋፋትን ለመግታት፤ በሌላ በኩል ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል ላይ ዘላቂ የሆነ የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ጅምሮቿ ለዓለም ተሞክሮ የሚሰጡ እንደሆኑ ያነሳሉ።

የዘንድሮው 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የአፍሪካ ኮፕ ቢባልም፤ አፍሪካ ውስጥ ከመደረጉ በዘለለ የአሕጉሪቱ ጉዳይ እንደ አቢይ ጉዳይ ተደርጎ አልተነሳም ይላሉ።

የአፍሪካ ሲቪክ ሶሳይቲዎች አሁንም ስለአፍሪካ ድምጻቸውን ሊያሰሙና ተጽዕኗቸውን ሊያጎለብቱ የሚገባ ሲሆን በተለይም በጉባዔው ላይ በሚካሔዱ ተጓዳኝ መድረኮች የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ህብረታቸውን አጠናክረው፤ 'ሽንጣቸውን ገትረው' ሊከራከሩ ይገባል ነው የሚሉት።

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የሰው ልጆች ሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፤ የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም አገራት፣ የሲቪክ ማህበረሰቦችና ግለሰቦች ዋና አጀንዳ መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።

አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ከልባቸው ግድ አልሰጣችውም የሚሉ ምሁራንም አልጠፉም። በየጊዜው የሚደረጉ ስምምነቶችን ገቢራዊ ለማድረግና ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድም ቁርጠኝነት እንደሚጎድላቸው ያነሳሉ። ለዘርፉ የሚመደበውን በጀት አጠቃቀም ላይም ችግር መኖሩን ይጠቅሳሉ።

የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረቶች ጥምረት የተሰኘው ድርጅት በጉባዔው ላይ "የአየር ንብረት አደጋ፤ የአፍሪካን ሕልውና ማረጋገጥ፣ ግስጋሴዋን ማስቀጠል" የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ይፋ አድርጓል።

መፅሐፉ  አፍሪካ ዘላቂ እና አየር ንብረትን መላመድ የሚያስችል የምግብ ስርዓት የምትመራበት የምግብ ፖሊሲ እንደሚያሻትም ትኩረቱን አድርጎ ያትታል።

አፍሪካ ብዝሃ የምግብ ስርዓት ቢኖራትም ዳሩ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የኢንዱስትሪ ወለድ ምግቦች እንደ መፍትሄ በመቅረባቸው ምክንያት ነባር የምግብ ስርዓቷ እየተቃወሰ መምጣቱንም ያነሳል።

በመላው አፍሪካ የሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ አሳ አስጋሪዎች፣ ነባር የማህበረሰብ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ ወጣቶችን ያማከለ የዳግም ትንሳኤ መንገድን ለመከተል ያስችላሉ ያላቸውን መረጃዎች ይዳስሳል።

ሁሉም የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂዎች ቢሆኑም በተለይም በአፍሪካ የግብርና ተዋናዮች ላይ እንደሚበረታም ነው የሚያነሳው። አሁናዊ የሰው ልጅ የግዴለሽነት እንቅስቃሴ ካልተገታ፤ ዓለም አቀፋዊ መፍትሄ ካልተበጀለት የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ ለአፍሪካ የሚያመጣው መዘዝ እየከፋ እንደሚሄድ ይጠቅሳል።

በሪፖርቱ መሰረት የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካን ምርት እስከ 20 በመቶ ይቀንሳል። ከ70 በመቶው በላይ ህዝቧ ዝናብ መራሽ በሆነ እርሻ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሕጉሪቱ ሕዝቦች በድርቅ፣ በከባድ ሙቀትና ሌሎች ተፈጥራዊ ቀውሶች አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ።

ይህም በድርቅና መሰል ቀውሶች ምክንያት አርሶ አደሮች ማሳቸው ጾም እንዲያድር፣ አሳ አስጋሪዎች መረባቸው ስራ እንዲፈታ፣ አርብቶ አደሮችም  እንስሳቶቻቸው መና እንዲቀሩ ያደርጋል፤ የአየር ንብረት መላመድ የሚያስችል መፍትሄ ካለተወሰደ በስተቀር።

የጥምረቱ የፕሮግራም አስተባባሪ ብሪጂት ሙጋምቤ እንደሚሉት እስካሁን በለጋሽና በመንግስታት እንደመፍትሔ የሚቀርቡ እርምጃዎች የአየር ንብረት ለውጥን ከመግታት ይልቅ ቀውሱን አባብሰዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም በመጠቆም።

ከኢንዱስትሪ የሚወጡ የግብርና ግብዓቶች ከመጠን በላይ የአፈርና የዕጽዋት ኬሚካል አጠቃቅም እንዲኖር በማድረግ በተለይም ለአፍሪካ ስነ-ምህዳር መዛባት ምክንያት እየሆኑ ነው ይላሉ።

የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረቶች ጥምረት የምንግዜም ቀዳሚ ሰለባ የሆኑ የአፍሪካ አርሶ አደሮች ዘላቂና የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል አማራጭን ያቀርባል። ይሄውም ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ግብርናን ወይም 'አግሮ ኢኮሎጂን' መከተል የአየር ንብረት ቀውስን ለመቋቋም አይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ያምናል። ለከባቢ አየር ብክለት የሚዳርጉ እንቅስቀሴዎችን መግታትም አልተዘነጋም።

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ጥምረቱ አርሶ እና አርብቶ አደሮችና አሳ አስጋሪዎችን፣ ሌሎች የገፈቱ ቀማሾችን ማስተባበር እና አደጋውን መቀልበስ፣ ቀውሱን መቀነስ ብሎም አፍሪካን ወደፊት እንድትገሰገስ ማድረግ ይገባል ነው የሚሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም