ቀጥታ፡

ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከአስረጅዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 1/ 2015 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ እንዳሉት በረቂቁ ላይ የተደረገው ውይይት አዋጁን ለማዳበር የሚያስችል ጠቃሚ ግብዓት ተገኝቶበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተልዕኮውን ከመፈፀም አንፃር ያጋጠመው ችግር ምንድነው? ስለፋይናንስና ስለግዥ ሥርዓት በረቂቅ አዋጁ ለምን አልተካተተም? በሚል ከምክር ቤት አባላት የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ከፍተኛ የህግ አማካሪዋ ወይዘሮ አለምነሽ ንጉሴ ለአስረጅዎች አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ተቋሙ የሚሰበስበውን ገቢ እንዲጠቀም ስላልተፈቀደለት በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራዎችን ለመሥራት እየተቸገረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሰይፈ አክለውም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ውስጥ ሰላሳ ስምንት ቅርንጫፎች እንዳሉት ጠቁመው፣ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ፣ የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛና የአረብኛ ቋንቋዎችን እየተጠቀመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመትም ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች በቻናል እንደሚወጣም አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ እንዳሉት በውይይት የተገኘውን ግብአት በማካተት የውሳኔ ሐሳብ አዘጋጅተው በቅርብ ቀን ለምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ በማቅረብ እንደሚያፀድቁ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም