የፍትህ ሚኒስቴር ከአምስት ተቋማት ጋር በወንጀል መከላከል መስክ አቅም ማጎልበት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ሚኒስቴር ከአምስት ተቋማት ጋር በወንጀል መከላከል መስክ አቅም ማጎልበት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 1/2015 የፍትህ ሚኒስቴር ከአምስት ተቋማት ጋር በወንጀል መከላከል መስክ አቅም ማጎልበት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
ሚኒስቴሩ ስምምነቱን የተፈራረመው ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት እና ከኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ጋር ነው።
ስምምነቱን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው ከየተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ህብረተሰቡ ወንጀልን ከመከላከል አንፃር በመስኩ ያለውን ግንዛቤ ለማጎልበትና ወንጀል ለመከላከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው።
ሚኒስቴሩ ተቋማት በአገሪቱ ሕጎች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወንጀል ከመከላከል አንፃር ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ህብረተሰቡ በሐገሪቱ ሕግ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዛሬው እለት ከአምስቱ ተቋማት ጋር እንደየ ስራ ባህሪያቸውና ተልዕኳቸው ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችሉ የህግ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲቻልም ስምምነቱ መፈረሙን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ስምምነቱ በጤናው ዘርፍ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በንቃተ ህግ ዙሪያ ለባለሙያዎች ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ ስምምነቱ በጤና ሚኒስቴር ስር ያሉ ሰራተኞች የንቃተ ህግ ማሳደጊያ ስልጠናዎች እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በመዲናዋ 832 በላይ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎቶች እንዳሉ የገለጹት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እነዚህ አገልግሎቶች ዋና ተልዕኳቸው ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው እለት የተደረገውም ስምምነት ኮሚሽኑ ለሚያካሒደው ወንጀልን የመከላከል ስራ ሰፊ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው ስምምነቱ ታራሚዎች የቅጣት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከህብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ከወንጀል እንዲርቁና ህግ አክባሪ እንዲሆኑ ንቃተ ህግ ይፈጥራል ብለዋል።
ስምምነቱ በተቋሙ ተረጋግጠው የሚሰጡ ሰነዶች ሀሰተኛ እንዳይሆኑ አስቀድሞ ለመከላከል ያግዛል ያሉት ደግሞ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ ናቸው።
ሐሰተኛ ሰነድ የአገር ልማትና እድገት ጸር በመሆኑ በዘርፉ ያሉ ሕጎችን ከማሳወቅና ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር ስምምነቱ ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ተወካይ ዶክተር ልጅአለም በጋሻው በበኩላቸው ስምምነቱ የህግ ትምህርት ቤቶች የዕውቀት መነሻ በመሆናቸው የህግ ዕውቀትን ከማስፋፋት አንፃር ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በዚህ መሰረት በንቃተ ህግ ማሳደጊያ ትምህርት እና ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት ስምምነቱ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።