በ2015 የትምህርት ዘመን ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ይሰጣል-ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በ2015 የትምህርት ዘመን ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ይሰጣል-ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 በ2015 የትምህርት ዘመን ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መስጠት እንደሚጀምር ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በትምህርት ሚኒስቴር የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ ዶክተር እዮብ አየነው ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ተደራሽነት ላይ ያለውን እጥረት ከመቅረፍ አንጻርም ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸውም ይገለጻል፡፡
ዶክተር እዮብ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ለዜጎች የሚያስብ፣ የሚሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ የሚወጣ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ330 በላይ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት እነዚህ ተቋማት በሚሰጡት የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በ2015 የትምህርት ዘመን ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ተማሪዎች ለምረቃ መብቃትና የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን መውሰድ የሚችሉት የመውጫ ፈተናውን ካለፉ በኋላ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የመውጫ ፈተና ዝግጅቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት እንደሚከናወንም አንስተዋል፡፡
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመውጫ ፈተና ዙሪያ ለሚያደርጉት ዝግጅት የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በ2015 የትምህርት ዘመን ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና መሰጠት እንደሚጀመር መገለጹ ይታወሳል፡፡