ቀጥታ፡

በደሴ የብረታብረት ኢንዱስትሪ ለተደራጁ ወጣቶች የ3 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጠረ - አስተዳደሩ

ደሴ (ኢዜአ) ህዳር 01 ቀን 2015 በደሴ የብረታብረት ኢንዱስትሪ ተደራጅተው ወደ ስራ ለገቡ ወጣቶች የ3 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ለኢዜአ እንደገለጹት የደሴ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ መለዋወጫዎችን በአገር ውስጥ በማምረት ለመተካት የተቋቋመ ነው፡፡

ኢንዱስትሪውን መልሶ የማጠናከር ስራ መሰራቱን የገለጹት አቶ ሳሙኤል፤ ወጣቶች አምርተው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ተደራጅተው እንዲሰሩ መደረጉን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ላመረቱት ምርት በዓመቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ እንደተገባ ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን የ3 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።

የደሴ ብረታብረት ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ ካሳው በበኩላቸው ድርጅቱ አሁን ላይ የመኪና ዕቃ መለዋወጫ፣ የዳቦ መጋገሪያ፣ የቡና፣ የሽንኩርትና የስጋ መፍጫ ማሽኖች፣ የኮንክሪት ፖል፣ የደረቅ ቆሻሻ ማስቀመጫና ማንሻ ገንዳዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማምረት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ከሚሰሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ጠይባ ሰይድ በኤሌክትሪካል ምህንድስና ተመርቃ ከጓደኞቿ ጋር በመደራጀት በፋብሪካው ስራ መጀመራቸውን አውስታለች፡፡

መስተዳድሩ ፋብሪካው ያለበትን ችግር በመፍታት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ለመጥቀም እንዳነሳሳቸው ተናግራለች፡፡

ስራ በጀመሩበት ወቅት ማሽኖቹ የማይሰሩ እና የገበያ ትስስርም እንዳልነበራቸው የገለጸው ወጣት ፋሲል እደግልኝ አሁን ላይ በፋብሪካው ውስጥ ማሽኖቹ በሚሰሩ በመተካታቸው ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልጿል።

አሁን ላይ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ገቢያቸውን ማሳደጉና ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቃቸውን ገልጿል፡፡

ከ8 ዓመታት በፊት በ52 ሚሊዮን ብር በተቋቋመው የደሴ ብረታ-ብረት ኢንዱስትሪ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ 50 ወጣቶች ተደራጅተው የተለያዩ መለዋዎጫዎችንና ቁሳቁሶችን እያመረቱበት እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም