የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ)ህዳር 1/2015 የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ አካሄዱ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ ፈርመዋል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደተናገሩት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተደራሽነታቸው ሰፊ በመሆኑ ለስራቸው ትልቅ አጋር እንደሚሆኑም ገልጸዋል ።
በቀጣይ ከሌሎች መሰል ድርጅቶችና ተቋማት ተመሳሳይ ስምምነቶች በማድረግ አብረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ “በዓለማችንና በኢትዮጵያ አከራካሪና አስቸጋሪ ጉዳዮች በሰለጠነ አካሄድ የመፍታት ልምድ አነስተኛ መሆን ችግሮች እየበዙ እንዲሄዱ እያደረገ ነው”ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት የችግሮች መፍቻ መንገዶች ቀጥታ ከውጭ የተቀዱ መሆን መፍትሄ አፈላለጉ ላይም የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፈፉን አንስተዋል።
ስምምነቱም የምክክር ኮሚሽኑ ችግሮችን ለመፍታት ህዝቡን ማወያየትና አካታች በሆነ መልኩ ለሚሰራው ስራ አዎንታዊና መርህ ተኮር ሚና ለመጫወት መሆኑን ተናግረዋል ።
የምክክር ኮሚሽኑ አሁናዊ የሀገሪቱ ችግሮችን የሚመጥን ምላሽ በመስጠት ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ሂደት ላይ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነው የገለፁት ።